እነኚህ የልማት እቅዶች ከተማዋ የአለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫነቷን ፤የአፍሪካ መዲናነቷን እና የሀገራችን ዋና ከተማነቷን የሚመጥን ገፅታና መልክ እንዲኖራት ፤ ብሎም ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ከከተማው እድገት ተቋዳሽና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስራ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ልዩ ትኩረት የሚሹ አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ ባለባቸው ስድስት ዋና ዋና ዘርፎች ለይቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
እነዚህም ፡-የቤት አቅርቦት ፤ የዳቦ አቅርቦትና ማእድ ማጋራት ፤የከተማ ግብርና፤የከተማ ፅዳትና ውበት ፤የአገልግሎት ማሻሻል፤ የእሁድ ገበያ ማስፋፋት ይገኙበታል፡፡
የቤት ጥያቄ በከተማችን አዲስ አበባ እጅግ አንገብጋቢ ከሆኑ ጥያቁዎች አንዱ ሲሆን በዚህ እቅድ ዝቅተኛውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፤ የግል ዘርፉን በማሳተፍና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚሰራ ነዋሪዎች ከከተማው እድገት ጎን ለጎን ህይወታቸው እንዲቀየር የሚያግዝ ነው፡፡
እናም የተጀመረው ያረጁ ቤቶችን የማደስ የበጎነት ተግባርም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ለየት ያለና ዘለቄታዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ የእድሳት ስራ የሚከናወን ይሆናል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተያዘው እቅድ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ጫናን ለመቋቋም እንዲያስችል በተለያዩ አካባቢዎች መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን በመገንባት ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የሚያስችል ስራ ነው፡፡
እንዲሁም የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ምርቶችን ለህዝቡ ለማከፋፈልም የመሸጫ ሱቆችን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋፋትም ከዚሁ ጎን ለጎን የሚሰራ ስራ ነው፡፡
በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን የመመገብ ስራም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ተጨማሪ አዳዲስ የምገባ ማእከላትን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በማቋቋም በተለይ ዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍል በኑሮ ጫና ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ያግዛል፡፡
የከተማ ግብርና ስራም በተለይ በመሃል ከተማ ዜጎች ቦታ የለንም በሚል ሳይወሰኑ ባላቸው አነስተኛ ቦታዎችና በተለይ (vertical farming) መንገድ በመጠቀም ነዋሪዎች ራሳቸውን መመገብ የሚችሉበት አማራጭ ነው፡፡
ከተማችን አዲስ አበባ የፀዳች የተዋበችና ለነዋሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን በልዩ ትኩረት ከሚሰሩ ስራዎች መሃከል ነው፡፡ ያማረችና የፀዳች ከተማ ለመፍጠር እንዲሁም ፅዳትን ባህል ለማድረግ በትጋት ይሰራል፡፡
የከተማችን አዲስ አበባን ደረጃ እና አለም አቀፍ ስታንዳርድ ለማሻሻል ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የከተማውን ህንፃዎች በዘፈቀደ የተቀቡ ቀለማትንና የሚገነቡ ህንፃዎችን ቁመት የሚወስን አለም አቀፍ ተሞክሮን የመተግበር ሃሳብ ነው፡፡
ይህም በአዲስ አበባ የሚታየውን ቡራቡሬ እና ዥንጉርጉር የሆነ እይታ ከብዙ አለም አቀፍና አፍሪካዊ ከተሞች ተሞክሮ በመውሰድ ለከተማችን የሚስማማ የህንፃ ቀለማት ስታንዳርድን ማስቀመጥ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ስራው ከመጀመሩ በፊት ሰፊ የጥናት ስራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን እንደ አዲስ አበባ 13 አይነት የቀለም አማራጮችን በማቅረብ የህንፃ ባለቤቶች ከቀረቡላቸው አማራጮች ውስጥ የፈለጉትን ወስደው የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ይህ ተግባር በሙከራ ደረጃ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በሂደት የስራው ድክመትና ጥንካሬ እየተገመገመ የሚሄድ ይሆናል፡፡
እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል ስራ ደግሞ በከፍተኛ ትኩረት ከሚከናወኑ ስራዎች አንዱ ነው፡፡ በየደረጃው የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ ከሌብነትና እጅ መንሻ የፀዳ አገልግሎ ለመስጠት በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎትም የማቀላጠፍ ስራ በልዩ ትኩረት በሚቀጥሉት ወራት የሚከናወን ይሆናል፡፡
አዲስ አበባን እንደ ስማ ውብና አዲስ እናደርጋለን!!