የአዲስ አበባ ከተማ አመሰራረት
አዲስ አበባ በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ህዳር 1879 ዓ.ም ተቆረቆረች፡፡ ከተማዋ ከባህር ዳር ወለል በላይ በሶስት ሺ ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የአየር ጠባይ ከብዘዎቹ የአለም ከተሞች እፍግ በጣም ተመራጭና ምቹ ለነዋሪዋም ሆነ ለቱሪስቶች ተስማሚ ነው፡፡ አዲስ አበባ በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ የላፓክ የኩይት ከተሞች በቅርብ በሶስተኝነት የምትመደብ በከፍተኛ ተራራ ላይ የተቀመጠች ዋና ከተማ ናት፡፡በተለያዩ ጊዚያትም በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን አስተናግዳለች፡፡ አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች አመሰራረት በተለየ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተቆረቆረችና ያለ ፕላን በዘፈቃድ የተስፋፋች ከተማ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አዲስ አበባ ባየዘመኑ የተከሰቱትና የአዲስ የስልጣኔ ውጤቶችን በመቀበልና በመላው ሃገሪቱ በማሰራጨት የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከመቆርቆሯ በፊት የአፄ ሚኒሊክ መቀመጫ ሆና ያገለገለችው በ1881 ዓ.ም እንጦጦ ነበረች፡፡ እንጠጠ በወቅቱ የተመረጠችው በዙያዋ ያሉትን ዝቅተኛ ቦታዎች ለሞቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም የቦታው አቀማመጥ ውጣ ውረድ የበዛበት በመሆኑ የማገዶ እንጨት፤የውሀና የምግብ እጥረት ተጨማምሮ ለንሮ አመቺ ባለመሆኗ ልትለወጥ ችላለች፡፡
አንዳንድ መዛግብት እንደሚያስዱት የእንጦጦ ብርድ የተፈታተናቸው እቴጌ ጣይቱ አየር ለመለወጥና ጠበል ለመጠመቅ ከእንጦጦ ወርደው ፍል ውኃ ላይ እንደሰፈሩና በአካካባቢው ቤት ለመስራት ለንጉሡ ጥያቄ አቅርበው ከፍል ውኃ ከፍ ብሎ በሚገኘው ቦታ ህዳር 1889 ዓ.ም ቤተ መንግሥት አሰርተው እንደተቀመጡና የአካባቢውን የኑሮ እና የሕይወት ተስማሚነት በመገንዘብ እቴጌ ጣይቱ “ፊንፊኔ” እየተባለች ትጠራ የነበረችውን ከተማ“ አዲስ አበባ” የሚል ስያሜ እንደሰጧት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም የእቴጌ ጣይቱ የሰፈራ ዕቅድ የመጀመሪያው የከተማዋ መሪ ኘላን ተደርጐ ተወስዷል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ሃገራችን የኢጣሊያን ጠላት ዓድዋ ጦርነት ድል እንድትቀዳጅ እንዲሁም በወቅቱ በተለያዩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ከተጫዎቷቸው ሚናዎች ባሻገር አዲስ አበባ ቋሚ የመንግሥት መቀመጫ እንድትሆንና የስልጣኔ መሰረት እንዲጣል በማድረጋቸው ባለውለታ መሆናቸው ይታወቃል፡
የአዲስ አበባ የሥልጣኔ አጀማመር
አዲስ አበባ ከ1886 እስከ 1931 ዓ.ም ድረስ ለዘመናዊ ከተማነት መልክና ቅርጽ መያዝ የትልልቅ ህንጻዎች መገንባትና ከተማዋን ወደ ስልጣኔ ማዕከልነት ያሸጋገሯት ክስተቶች ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ እንጦጦ ላይ ከተቆረቆረች ጊዜ ጀምሮ ጉልህ የስልጣኔ ተግባራት ተከስተዋል፡፡ በአክሱም ነገሥታት ከታተሙት የመገበያያ ሳንቲሞች በኃላ ብሔራዊ ገንዘብ ታትሞ ለዝውውር የበቃውና የቴሌፎን አገልግሎት የተጀመረው በ1986 ዓ.ም ነው፡፡
በ1902 የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በ1890 የሩስያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል ተመስርተዋል፡፡ በ1894 የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ኩባንያ፣ በ1897 የአቢሲንያ ባንክ፣ 1898 ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት፣ በ1900 የእቴጌ ጣይቱ ሆቴልና የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት፣ በ1916 ዓ.ም ሥራቸውን የጀመሩበት ዓመታት እንደሆነ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ የዘመናዊ መንገድ መሥራት፣ የመኪና መምጣት፣ የቧንቧ ውሃ መዘርጋት፣ የኢትዮጵየ አየር መንገድ መመስረት፣ የትላልቅ ህንጻዎች መገንባት፣ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት፣ ዩንቨርስቲዎች መከፈት፣ የጤና ተቋማት መበራከት ፣ የመንግሥት አስተዳደር ቅርጽ አያያዝ መምጣት አዲስ አበባን ወደ ስልጣኔ ማእከልነት ያሸጋገሯት የዘመኑ ክስተቶች ናቸው፡፡

