ኢትዮጵያ ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ የኮንኮ ኪንሻሳ የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ መግለጫ አውጥታለች ።
ከመግለጫው የተወሰደ ፦”…የታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዓመት ሙሌት በመርሆዎች መግለጫ መሰረት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይከናወናል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በግድቡ የሁለተኛ ዓመት ሙሌት ዙሪያ ተገቢውን መረጃ ለመቀያየር ዝግጅቷን በተደጋጋሚ ገልፃለች። ሁለቱ ሀገሮች ስምምነት ሳይደርስ ግድቡ መሞላት የለበትም በሚል የሚቀርብ አቋም የህግ መሰረት የሌለው እንዲሁም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። የግድቡ አሞላል እና ተያያዥ የውሃ አለቃቅ ስርዓት ላይ ለመስማማት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዝግጁ ብትሆንም ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር እና ውጤቱ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብ እና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያጸና አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል ግትር አቋም ይዘዋል።ኢትዮጵያ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የሆነ የአሁን እና የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚያቅብ ማናቸውም ዓይነት ስምምነት አትፈርምም፡፡