የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ትላንት የተባበሩት መንግስት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ወጥ የሆነ አቋም ማንጸባረቁ ለኢትዮጲያም ፤ለአፍሪካም ድርብ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ይዛ የተነሳችዉን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ” የማምጣት መርህ አሳክታለችም ብለዋል።
አንጋፋው የአፍሪካ ህብረትም የሀገራቱን የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ጉዳያቸዉን እንዲመለከት የፀጥታው ምክር ቤት መምራቱ አፍሪካውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መንገድ መፍታት ይችላሉ የሚለዉን ትርክት በመፍጠር በራሱ ለመላው አፍሪካውያን ትልቅ ድርብ ድል ነዉም ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።
“በትላንት ምሽቱ እልህ አስጨራሽ ክርክር የተሳተፋችሁ፣ ገና ከስብሰባው አስቀድሞ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስሪያቤት በመገኘት በፍጹም የአገር ፍቅር ስሜት የኢትዮጵያን የእዉነት ድምፅ ያሰማችሁ የሀገሬ ልጆች፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ተሳታፊ የሆናችሁ፣ ይህንን በደምና በአጥንት የቆመ ግድብ ከሰርጎ ገቦች ሌትና ቀን በንቃት የምትጠብቁ የፌደራል ፖሊስ እና የጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በሙሉ፤ እንዲሁም ከመቀነታቸዉ፣ ከደሞዛቸው እና ከከረሜላ መግዣቸዉ ጭምር ለግድቡ ግንባታ እያዋጡ ያሉ አረጋዉያንና አቅመደካሞች፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ ህፃናትና ባለሀብት ነጋዴዎች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁም” ብለዋል፡፡