አቶ ጃንጥራር አባይ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ
ቢሮዉ የዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዪ የመስሪያ ቦታዎችን እየገነባ ለተጠቃሚዎች እያስተላለፈ ይገኛል ፡፡
በዛሬዉ እለት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከዚህ በፊት በተለያየ ምክንያት አገልግሎት ያልሰጡ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ እና ከዚህ በፊት ለተጠቃሚ ተላልፈዉ 5 አመት አገልግሎት የሰጡ የመስሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች በእጣ አስተላልፏል፡፡
በዚህም 102 ኢንተርፕራይዞችና 450 አንቀሳቃሾች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ዉስጥ 55% ተጠቃሚዎች ሴቶች ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ የአካል ጉዳተኞች እና ከስደት ተመላሾች በእጣዉ ተካተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከተማችን በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙባት እንደመሆኗ መንግስት ስትራቴጂ በመንደፍ የመስሪያ ቦታዎችን ገንብቶ ማስተላለፍን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል ::
ይሁን እንጂ መንግስት ለሁሉም የመስሪያ ቦታ ገንብቶ ማስተላለፍ ስለማይችል ስራ ፈላጊዎችን ከተለያዩ ድርጅቶችና ፋብሪካዎች ጋር ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል፡፡ አቶ ጃንጥራር አያይዘዉም የዛሬ እድለኞች የወሰዱትን የመስሪያ ቦታ በአግባቡ ከህገ-ወጥ ድርጊት በመቆጠብ እንድትሰሩበት በማለት የዘርፉ አመራሮችም በቀጣይ የመስሪያ ቦታዎችን ለሚመለከተዉ ተጠቃሚ በፍትሀዊነት እንድታስተላልፉ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡