ዛሬ ልጇ ሶስተኛ ዓመቷን እያከበረች ነው። እናት ግን ኬክ አሊያም የልደት ሻማ ይዛ ወደቤቷ አልሄደችም፤ ይልቁንም ከመከላከያ የተሰጣትን ግዳጅ ለመፈጸም ጭነቷን አስተካክላ በልበ ሙሉነት ጉዞዋን ወደግንባር አድርጋለች።
የመከላከያ ከባድ ተሽከርካሪ ሾፌሯ ሰሚራ ይማም የሁለት ልጆች እናት ነች። አንዱ ልጇ አስር ዓመቱ ሲሆን ትንሿ ልጇ ደግሞ ዛሬ ነው ሶስትኛ ዓመቷን የያዘችው።
እናት በሰሜን ወሎ ግንባር ለተሰለፈው ጥምር ጦር አስፈላጊውን ስንቅና ትጥቅ በማመላለስ ስራ ላይ ተጠምዳለች። “ስካኒያ” የተሰኘውን ተሳቢ ተሽከርካሪ በልበ ሙሉነት እያሽከረከረች ከግንባር ድረስ ዘልቃ አስፈላጊውን ግብዓት ታደርሳለች።
ዛሬ ሴት ልጇን አቅፋ እየሳመች ልደቷን ልታከብርላት ባትችልም፤ ለአገርና ለሕዝብ ፍቅር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል በሙያዋ እያገለገለች በመሆኑ “ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
“ወደመከላከያ የገባሁት መንግስት በየሙያችሁ የምታገለግሉ ብሎ ጥሪ ሲያቀርብ ነው” የምትለው ሰሚራ፤ በወቅቱ በፍቃደኝነት መቀላቀሏን ታስታውሳለች።
ልጆቿን ለእህቷ ልጅ እንድትንከባከባቸው ሰጥታ የቤት ኪራይና አስፈላጊውን ወጪ እየሸፈነች ታስተዳድራለች። በተጨማሪነት አንድ የእህቷን ልጅም ከልጆቿ ጋር አብራ ታሳድጋለች።
“አሁን ላይ ስለጆቼ ሳይሆን ይበልጥ ስለሀገር የማስብበት ጊዜ ላይ ነኝ” የምትለው ሰሚራ፤ “ልጆቼ አገር ሰላም ስትሆን የበለጠ ደስተኛ ሆነው ያድጋሉ። እስከዚያው ድረስ ግን እኔም በሙያዬ የበኩሌን መወጣት አለብኝ” ስትል በሥፍራው ለሚገኙት የኢፕድ ዘጋቢዎች ተናግራለች።
መከላከያን ከተቀላቀለች አንድ ዓመት የሞላት የከባድ መኪና አሽከሪዋ ሠሚራ፤ በሙያዋ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ግንባሮች ላይ መሰማራቷን ነው የምትገልጸው።
ባለችበት ግንባር አስፈላጊውን ጭነት ካመላለሰች በኋላ አረፍ ባለችበት ወቅት ለልጇ ልደት ይህንን መልዕክት አስተላልፋለች፤
“እናትሽ ሰሚራ ትወድሻለች፤ ልጄ መልካም ልደት እመኝልሻለሁ፤ አገር ሰላም ስትሆን ደግሞ አብረን በጋራ እናከብራለን” ስትልም ነው ለልጇ መልካም ምኞቷን የገለጸችው።