አዲስ አበባ 4 ሚልዬን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ 4.5 ሚልዬን በላይ በመትከል ደማቅ ታሪክ ጻፈች!
ከአንድ ሚልዬን በላይ የአዲስ አበባ ህዝብ የክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድን ጥሪ ተቀብሎ የማለዳው ዝናብና ቁር ሳይበግረው በነቂስ ወጥቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 ሚሊዮን ችግኝ ባንድ ጀምበር የመትከል መርሀ ግብር ላይ 4.5 ሚልዬን በላይ በመትከል የድርሻውን በብቃት ተወጥቷል ፡፡
የመንግስት ፣ የግል ፣ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሰራተኞች ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መምህራን ፣ የጤና ባለሙያዎች ፣ ተማሪዎች ፣ የፀጥታ አካላት ፣ ሴቶች ፣ የከተማችን ወጣቶች ፣ ባለሃብቶች ፣ አርቲስቶች ፣ የስፖርት ቤተሰቦች ፣ የሚዲያ ባለሞያዎች ፣የአካል ጉዳተኞች፣ ህፃናት፣ ሙሽሮች ፣ አባት አርበኞች፣አዛውንቶች፣ እመጫቶች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አምባሳደሮች ፣ ዲፕሎማቶች ፣ አለማቀፍ ማህበረሰቡ ጭምር ባዘጋጀንላቸው ስፍራ ደማቅ ተሳትፎ አድርገዋል ::
የከተማችን ነዋሪ ታላቅ ታሪክ ሰርቷል!
አምና በአንድ ጀንበር 3 ሚልዬን ተክለን ነበር ዘንድሮ 4.5 ሚልዬን በላይ በመትከል የራሳችንን ክበረ ወሰን ሰብረናል ::
በመተባበራችን ለመጪው ትውልድ የተፈጥሮ ሚዛኗ የተጠበቀ ለኑሮና ለስራ የተመቸች አዲስ አበባን መገንባት የሚያስችለንን ታላቅ ስራ ሰርተናል፡፡
ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ችግኝ በማዘጋጀት በማጓጓዝና ጉድጓድ በመቆፈር ፤በችግኝ ተከላ የተሳተፋችሁ የከተማችን ነዋሪዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ደስ አለን!
ለዚህ ስኬት ለተባበራችሁ ሁሉ በራሴና በከተማው አስተዳደር ስም ከታላቅ አክብሮት ጋር ከልብ አመሰግናለሁ::
አዲስ አበባ ታመሰግናለች!
በቀጣይ የተከልነውን በመንከባከብ እና ለፍሬ በማብቃት በትጋት ማገልገልችንን እንቀጥላለን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ