ከሁሉም አካባቢዎች ለወሰን ማካለል ስራው የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመተንተን ከውሳኔ ለመድረስ 7 ዓመታት መፍጀቱን የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ገለጹ።
ጥናትን መሰረት አድርጎ የተከናወነው የወሰን ማካለል ስራው አዲስ አበባንም ሆነ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን የወሰን ማካለል የቴክኒክ ኮሚቴው አባላት ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ከሁለቱም በኩል አምስት አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ መረጃዎችን ከሁሉም አካባቢዎች የማሰባሰብ እና የመተንተን ስራ መስራቱን የሚናገሩት አባላቱ ፣ይህም 7 ዓመታትን መፍጀቱን ተናግረዋል።
የወሰን ማካለል ስራው አዲስ አበባንም ሆነ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን በማይጎዳ መልኩ፣ በህግና ስርዓት ማዕቀፍ ሆኖ ማደግ እንዳለበት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ሀርገሞ ሀማሞ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት ሲሰፋ አርሶ አደሮች የልማቱ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ መሆን የለባቸውም ያሉት አቶ ሀርገሞ ፣ከእድገቱም በፍትሃዊነት ሁሉም መጋራት አለባቸው ብለዋል ።
የወሰን ማካለል ባለመኖሩ ምክንያት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል በ3ሺ ሄክታር መሬት ላይ የካርታ መደረራብ እንደነበረ የገለጹት ሌላው የቴክኒክ ኮሚቴው አባል አቶ ግፋወሰን ደሲሳ ፣ የወሰን ስራው መከናወኑ ይህን ችግር ይቀርፋል ብለዋል።
የነበረውን የወሰን ችግር ተጠቅመው የኪራይ ሰብሳቢዎች መደበቂያ፣የመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠሪያ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እንደነበረ ገልጸዋል።
የወሰን ማካለል ስራው የሁለቱን አስተዳደር ህዝቦች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን አይገድበውም ያሉት የኮሚቴ አባላቱ፣ለአስተዳደራዊ አገልግሎት በሚመች መልኩ ልማታቸውን ፣የመልካም አስተዳደር ጉዳያቸውን እንዲፈጽሙበት ብቻ በህግ ተወስኖ የተሰጠ አካባቢ አመላካች መስመር ነው ብለዋል።#ebc