ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ሰጥተዋል::
በ2014 የትምህርት ዘመን ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 896,520 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ600 በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 273 ሲሆን ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 125 ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ መሆናቸው ታውቋል::
በእውቅና መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች ትልቁ ኢንቨስትመንታችን በሆነው ትምህርት ያሰብነው ውጤት ባይመጣም ዛሬ የሸለምናችሁ በፈተና ውስጥ ያለፋችሁ እንቁዎች ስለሆናችሁ ነው ብለዋል።
የተገኘው ውጤት የሚያሳየው ገና ብዙ መስራት የሚጠበቅብን በመሆኑ በቀጣይ ከዚህ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርት ባለድርሻ አካላት, መምህራን, ወላጆች እንዲሁም ተማሪዎች የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲወጡ ከንቲባ አዳነች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል::
ከአጠቃላይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 3.3% መሆኑ ይታወቃል:: በአዲስ አበባ ከተማ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል በአንፃራዊነት አበረታች ሊባል በሚችል መልኩ 19.8% ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃቸውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል::