የጦር መሳሪያዎቹ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ/ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በተለምዶ ሃና ማርያም ቀጠና 3 ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተሸሽጎ ነው።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የተወርዋሪ ኃይል ሻለቃ 2 ምክትል ሻለቃ መሪ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ጎሳ ከድር እንደተናገሩት ከአካባቢው ህብረተሰብ ለፀጥታ አካላት በደረሰው ጥቆማ ፖሊስ የፍርድ ቤት መበርበሪያ ትዕዛዝ በመያዝ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ባደረገው ብርበራ 21 ፋልኮት፣ 6 የቱርክ ሽጉጦች፣ 245 የሽጉጥ ጥይት፣ 78 የክላሽ ኮቭ ጥይት፣ 4 የክላሽ ካርታ፣ 4 የክላሽ ማህደር እና 1 የክላሽ ሰደፍ ከሁለት ተጠርጣሪዎቹ ጋር መያዛቸውን ገልጸዋል። የከተማችንን ሠላምና ደህንነት ለመጠበቅ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት እያሳየ ያለውን ተባባሪነት አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል።