የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው ለዜጎች ሰላም መረጋገጥ እንዲሁም የቁልፍ መሰረት ልማቶችን ደህንነት በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመጠበቅና ስጋቶችን ለመከላከል ሲባል ድሮኖችን ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ ለቀረፃ መጠቀምም ሆነ ማብረር እንደማይቻል ማሳሰብ ይወዳል፡፡
አንድ አንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚመለከተው አካል ህጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ድሮኖችን በሀገሪቱ በሚካሄዱ ሃይማኖታዊ፣ባህላዊ እና ህዝባዊ ሁነቶች ላይ ለቀረፃ ሲጠቀሙ እና ሲያበሩ እየተስተዋለ መሆኑን ያመለከተው አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ፤ ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አውቀው ከህገ ወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኘ ድሮኖችን ለቀረፃ ሲጠቀም እና ሲያበር የተገኘ ማንኛውም አካል ወይም ግለሰብ በህግ እንደሚጠየቅ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከወዲሁ ለህብረተሰቡ መግለጽ ይወዳል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት