ከተማዋ በክረምት ወቅት ሲሰሩ የቆዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በማጠናቀቅ በበጋ ወቅትም ቀጣይነት እንዲኖረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
ከ246 ሽህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍና በክረምት የተገኘውን ልምድ በበጋ ወቅትም በማስቀጠል የተሻለና ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ነው የአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር የተናገሩት፡፡
የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ በማጋራት፣የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ከግል ባሃብቶችና ድርጅቶች ጋር በትስስር ለመስራት መታቀዱንም ነው የገለጹት።
የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከ353 ሽህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3 ሽህ ቤቶችን በማደስ አረጋውያን፣አካል ጉዳተኞችን የሀገር ባለውለታዎችን ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህም ከ2 ቢሊየን ብር በላይ መንግስትን ከወጪ ማዳን እንደሚቻል ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ተናግረዋል፡፡
የ2015 የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በነገው እለት በይፋ በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚጀመር ሲሆን የግል ባለሃብቶች፣ መንግስራዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገንዘባቸውና በጉልበታቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የሃገር ባለውለታዎችን በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀንበር ጠይቀዋል፡፡