ከተለያዩ ከተሞች እና ተቋማት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን የካይሮ ከተማን የሕዝብ ብዛት መጨናነቅ ለማስተንፈስ መልሶ የማልማት እና ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ዘመናዊ፣ ሁለገብ እና ምቹ ከተማን ለመገንባት የተሠሩ ሥራዎችን እንዲሁም ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት፤ ገጠርን ከከተማ አስማምቶ ለማደግ የተከናወኑ ተግባራትንም ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ወቅት ከካይሮ ከተማ አስተዳደር ጋር ከተሞችን በማዘመን፣ ወቅቱን የዋጀ የከተማ እና የመሠረተ ልማት ግንባታን፣ እንዲሁም የተጨናነቁ የከተማ አካባቢዎችን ስለማስተካከል በተሠሩ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጏል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በባህል፣ በታሪክ እና በሕዝብ ብዛት ተቀራራቢነት ያላቸው በመሆኑ የልዑካን ቡድኑ ያገኘው ልምድ በየከተሞቹ ሊተገበሩ የሚችሉ መሆናቸውን አባላቱ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ ፣ የፌዴራል አመራሮች እንዲሁም የአዳማ፣ የባሕር ዳር እና የሐዋሳ ከተሞች ከንቲባዎች ተሳትፈዋል።
ጉብኝቱ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በግብጽ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተከናወነ ነው::