ከጽንስ እስከ ስድስት አመት ዕድሜ ያሉ ሕጻናት በአዕምሮና በአካል እንዲበለጽጉ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ከንቲባ አዳነች ዛሬ ባስጀመርነው ንቅናቄ እናቶች አስዳጊዎች እና ባለድርሻ አካላት በሕጻናት አስተዳደግ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል::
ለዚህም እንዲያመች በዛሬው ዕለት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርታችንን ለማሸጋገር የሚያስችል በጥናት እና ምርምር ላይ የተደገፈ ስራ ለመስራት ከግዙፉ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርመናል ያሉት ከንቲባ አዳነች 1400 በሕጻናት እንክብካቤ የሰለጠኑ ባለሙያዎች መመረቃቸውንም ገልፀዋል::
አስተዳደራችን በሀገራችን የመጀመሪያውን የቀዳማይ ልጅነት ፍኖተ ካርታ አጽድቆ ስራ ጀምሮአል ያሉት ከንቲባ አዳነች በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የህጻናት ማቆያና ተንከባካቢ ባለሙያዎች ይመደባሉ ብለዋል::
በሚቀጥሉት ሶስት አመታት 12 ሺህ የህጻናት መጫዎቻ ስፍራዎች ለማዘጋጀት እየሰራ ያለው ከተማ አስተዳደሩ 59 የሚሆኑትን ዘንድሮ አጠናቅቆአል::
በቀዳማይ ልጅነት ሳምንት በሕጻናት አስተዳደግ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የሚሰሩ ይሆናል::
አዲስ አበባን ሕጻናት ለማሳደግ ምርጥ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ እንሰራለን!