ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክ/ከተማ በተለምዶ ጌጃ (ከረዩ) ሰፈር ተብሎ በሚጠራውና ሰፊ ድህነትና ጉስቁልና በሚታይበት አካባቢ የ G+5 የመኖርያ ቤት ግንባታ በዛሬው እለት አስጀመዋል::
በዚሁ ስነስርዓት ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት በዚህ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን ተስፋ ለማለምለም፤ በኑሮ ውድነትና በቤት እጦት የሚሰቃየውን ህዝብ በምንችለው ለማገዝ ጥረት እያደረግን ሲሆን ውጤቱም እየታየ ነው ብለዋል፡፡
በተለምዶ ጌጃ (ከረዩ) ሰፈር ሙሉ ለሙሉ ሞዴል አድርጎ ለመውጣት በምገባ ማእከል ፤የመኖርያ ቤት ፤የመስርያ ቦታ ፤የከተማ ግብርና አጠቃላይ ስራዎች ተሳልጦ እየሄደ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወጪውን የሚሸፋነውን የብዙአየሁ ታደለ ፋውንዴሽን አመስግነዋል:: የአካባቢው ነዋሪ ፤እንኳን ልማት መጣልን ብሎ አብሮ እየሰራ በመሆኑ የሚበረታታ ደግባር መሆኑን ገልፀዋል ::
በዚሁ አጋጣሚም ሌሎችም ባለሃብቶች አብረውን እየሰሩ ካሉት ባለሃብቶች ተሞክሮ በመውሰድ ለአካባቢያችሁ የምትችሉትን ታደርጉ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ የብዙአየሁ ታደለ ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ‹‹ከተለመደው የግንባታ ሂደት ወጣ ያለ ዘመናዊና ያማረ ስራ እንደምንሰራ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ›› በማለት ገልፀዋል፡፡
የልደታ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሰግደው ሀ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ነድፈን እየሰራን ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በልደታ ክ/ከተማ በ60 ቀናት የጓሮ አትክልት ልማት ስራዎች የደረሱ አትክልቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ የማእድ ማጋራት አከናውነዋል፡፡