ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ የእንጀራ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ይህ ፋብሪካ 1000 ሺህ የእንጀራ ምጣድ የሚኖረው ሲሆን እስከ 4 ሺህ ለሚደርሱ እናቶችና ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር እና በ3 ወር ውስጥ ተገንብቶ ወደ ስራ እንደሚገባ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ፋብሪካው በቀን እስከ 3.4 ሚሊዮን በዓመት እስከ 1.3 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያመነጭ ይሆናል፡፡
በዚህ በሃገራችን የመጀመርያ የሆነው ግዙፍ የእንጀራ ፋብሪካ የግብይት ሰንሰለቱን ጠብቆ በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች የጤፍ ምርት በመግዛት የሚጠቀም ሲሆን የእንጀራ ምርት ለአለም አቀፍ ገበያም ኤክስፖርት ለማድረግም በእቅድ ተይዟል፡፡
ፋብሪካው እንደ ማሰልጠኛ የሚያገለግልም ሲሆን ሴቶች ራሳቸውን እየቻሉ ወደሌላ የስራ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ክህሎት እያስጨበጠ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ‹‹ ይህ ፕሮጀክት የ2015 ዓ.ም የገና በዓል ለእናቶች የተበረከት ሥጦታ ነው ብለዋል፡፡ ›› እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ብለን የጀመርነው ስራ ያለ እንጀራ ሌማት ሊሞላ አይችልም ብለዋል፡፡ የሚሠሩ እጆች እንዲበረክቱ በማድረግ እና በዙሪያችን ያልተጠቀምንባቸው ፀጋዎችን በመጠቀም መለወጥ የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች ጨምረውም እኛ ኢትዮጵያውያን ካልሠራንና ካልተጋን ለውጥ ይመጣል ብሎ መሠብ ሞኝነት ነው ስለዚህ አብረን ሠርተን በጋራ እንለወጣለን ብለዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ሮባ በበኩላቸው በክፍለ ከተማችን እንዲህ አይነት በርካታ ስራ አጥ የሆኑ እናቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች መበራከታቸው ስራዎች በላቀ ተነሳሽነት ለመስራት አቅም ይሆናል ሲሉ ይህ ፕሮጀክት በአስተዳደሩ መጀመሩ የበርካታ እናቶችን ድካም የሚቀንስና በኢኮኖሚ ረገድ ገቢን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላልም ብለዋል።
ግንባታውን የሚያከናውነው የኦቪድ ግሩብ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ኢንጅነር ዮናስ ታደሠ አለማችን ልማት ነው ያሉት ኢንጂነር ዮናስ በስራዎቻችን በሀገራችን በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው በመሆኑም ይህ ፕሮጀክት በሦስት ወራት አጠናቀን ለተጠቃሚዎች እናስረክብ ዘንድ አስተዳደሩና ነዋሪው ለስራቸው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል።