ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የትምሕርት ቤቶች እና የጤና ፕሮጀክቶችን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል::
በምርቃ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቶቹ የህብረተሰቡን አዳጊ ፍላጎትና መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚመልሱ ፣ ለህዝብ የገባነውን ቃል መተግበራችንን የሚያሳዩ እንዲሁም ሁሌ በሰራነው ሳንረካ ይልቁኑ በተገኘው ውጤት እየበረታን የህዝብ አገልጋነታችንን በተግባር የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል::
ፕሮጀክቶቹ ለትውልድ ግንባታ ስራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተገነቡት 72 የትምህርት ፕሮጀክቶች የተማሪ ክፍል ጥመርታን በማሻሻል ጥራት ያለው ትምህርትን ለማድረስ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
የጤና ዘርፉን አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እና ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን አሁን ለምረቃ የበቁ ፕሮጀክቶችም የጤና ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ከንቲባ አዳነች ጨምረው ገልፀዋል።