የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ50 ቢሊዮን ብር ወጪ በመቻሬ ሜዳ በ250ሺ ካ/ሜ መሬት ላይ ለሚያስገነባው “መሐመድ ኢያ ቪሌጅ” የመኖሪያ መንደር ግንባታ ከንቲባ አደነች አቤቤ የመሠረት ድንጋይ በዛሬው ዕለት አኑረዋል
በመረሀ-ግብሩ ላይ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ፣ የሚዲሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድን ጨምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ፕሮጀክቱን በጋራ ጀምሮ ለመጨረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመኖሪያ መንደር ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ለከተማችን መዘመንንና ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ የላቀ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ለስኬታማነቱ ልክ እንደ መንግስት ፕሮጀክት የምንከታተለው ይሆናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በከተማችን አዲስ አበባ ሌላ መለስተኛ ከተማ ከመገንባት ጋር የሚተካከል ግዙፍ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት መሆኑን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
አጠቃላይ የልማት ሥራዎች መንግሥት ብቻ ሊሰራ አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች የግሉ ሴክተር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ አጠቃላይ ሀገር አቀፍ የልማት ሥራ ውስጥ ተደማሪ እንቅስቃሴ ልያደርግ ይገባል ብለዋል ከንቲባዋ
የሚዲሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትም ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ሰዓት እየተከናወነ ካለው የፕሮጀክት አፈጻጸም ልምድ በመውሰድ ይህንን ግዙፍ ፕሮጄክት በተያዘለት ግዜ አጠናቆ ለፍሬ ያበቃል የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ ብለዋል ከንቲባዋ ።
ቀኑ የአንድነት ቀን እንደመሆኑ መጠን አንድነታችን ኃይላችንና የአሸናፊነታችን ዘመናትን የተሻገረ ምልክት በመሆኑ አጽንተን ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል ከንቲባዋ
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ በመረሀ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ውስጥ ሌላ አነስተኛ ከተማ እንደገነባን የሚቆጠር ዓለም የደረሰበትን ስልጣኔና ቴክኖለጂ አሟልቶ የሚገባ በመሆኑ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ከፕሮጀክቱ ወጥን አንስቶ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉልን በመሆናቸውና ዛሬም የመሠረተ ድንጋይ ለማኖር በመካከላችን ስለተገኙ እናመሰግናቸዋለን ብለዋል
የሚዲሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚያስገነባው ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ዲዛይን የተደረገና የሚገነባ ግዙፍ የመኖሪያ መንደር ፕሮጀክት መሆኑን አቶ መሐመድ ጨምረው ገልጸዋል