አንጋፋውና በኢትዮጵያ የጥበብ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው፤ በርካታ አንጋፋ አርቲስቶችን ለሃገራችን ያበረከተው የራስ ቲያትር ቤት አዲስ ግንባታ ዛሬ በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለታል፡፡
ለከተማችን የአርት ስራ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር ቤት ግንባታ እንዲሁም ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ህፃናትና ወጣቶችን ቲያትርና ሃገር ፍቅር ቲያትር ቤቶችን ግንባታ ወደ ማጠናቀቁ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በዛሬው እለት በግንባታ መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ላይ ታዋቂዎቹ አንጋፋዎቹ የኪነጥበብ ሰዎች፤ በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ውጣ ውረድ ውስጥ ትልልቅ ዋጋ የከፈሉ አርቲስቶች ተገኝተዋል
በመሰረት ማስቀመጥ ስነስርዓት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለኪነጥበቡ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመስራት ላይ እንገኛለን ፤ በከተማችን አስር አምፊ ትያትሮችን በማስገንባት ፤ የማዘጋጃ ቤቱ የባህል አዳራሽ ባማረ መልኩ የገነባን ሲሆን ዛሬም እነሆ የመጀመርያውን አዲስ ትያትር ቤት ግንባታ መሰረት ድንጋይ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡
የማንጨርሰውን አንጀምርም፤ የጀመርነውን እንጨርሳለን ያሉት ከንቲባ አዳነች ጥበብ ትውልድን በመቅረፅና በመገንባት ትልቅ ሚና ስላላት አሁንም ትኩረት ሰጥተን መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
እናንተም ጥበባችሁን ተጠቅማችሁ አገር ግንባታ ላይ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ላይ በርትታችሁ ስሩ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡