ብቸኛ የህዝብ አደባባይ የነበረውን የመስቀል አደባባይ የሚደግም ሁለተኛ ታላቅ ፕሮጀክት በ1.3 ቢሊዮን ብር በጀት በዛሬው እለት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በይፋ ተጀምሯል፡፡
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ውጪ ሃገር ያሉ ፕሮጀክቶችን ስንመለከት ለሃገራችን ብለን እንመኝ ነበር ያሉ ሲሆን ነገር ግን በመመኘት ውጤት አይመጣም በመስራት ነው እንጂ ብለዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት መሃል ከተማ ያሉ ብቻ ናቸው የሚዋቡ የሚለውን ምላሽ የሚሰጥ ነው ዳር ላሉ የከተማዋ አካባቢዎችም እንዲህ አይነት ስፍራ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
መስቀል አደባባይ በሚመረቅበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፊት መልዕክት ተጨማሪ መስቀል አደባባዮች ለከተማዋ ያስፈልጓታል ብለው በተናገሩት መሰረት ቃላቸውን ፈፅመን ይህን ፕሮጀክት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ እናስቀምጣን ብለዋል፡፡
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ቦታው የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት አዲስ አፍሪካ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እዚህ አካባቢ እየተገነባ ያለ በመሆኑ ነውና አከባቢው ተጨማሪ አገልግሎቶችና ተያይዘው የሚመጡ ስፍራዎች የሚያስፈልጉት መሆኑንም አውስተዋል፡፡
በአሮጌ ወይም ባለፈበት አስተሳሰብ ከተማችን ልንቀይር አንችልም ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከዘመኑ ጋር የዘመነ አሰራርና አስተሳሰብ በመያዝ ነው መቀየር የሚቻለው በመሆኑም የግሉን ሴክተር በማሳተፍ የመንግስትን ክፍተት በመሙላት እና በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ 14ሺህ 400 ካሬሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን የህዝብ ስፍራ አደባባይ (public space) የመኪና ማቆምያ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ጂምናዝየሞችን፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የህዝብ መሰባሰቢያ ስፍራ (public space)፣ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ፣ የሰርግና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ፣ ሱፐርማርኬት፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች፣ መጽሀፍት የማንበቢያ ስፍራና የመሳሰሉት ይኖሩታል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በግንባታው ወቅት እስከ 1100 ያህል ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን በቀጣይ በቋሚነት ለ400 ዜጎቻችን የስራ ቦታቸው የሚሆን ነው፡፡
ስራው 18 ወራት መውሰድ ሲገባው ሌትና ቀን ያለ እረፍት በመስራት በ10 ወራት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች የተናገሩ ሲሆን በጋራ ሃላፊነት አብሮ በመስራት እና በመተባበር ያሰብነውን ፕሮጀክት እውን ማድረግ እንችላለን በማለት ተናግረዋል፡፡