ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በ60 ቀናት ፕሮጀክት በልዩ ሁኔታ በሚደግፉት የልደታ ክ/ከተማ እጅግ የተጎሳቆለውና ለኑሮ አስቸጋሪ የሆነው ጌጃ ሰፈር (ከረዩ) አካባቢ ከሚተገበሩ ሞዴል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች መሃከል በዛሬው እለት ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን መመገብ የሚችለውን እንደ ከተማ 7ኛውንና ትልቁን የተስፋ ብርሀን ምገባ ማዕከል መርቀው የከፈቱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በቦታው የነበሩ ጎስቋላ ቤቶችን መልሶ በመገንባት 8 ዘመናዊ የመኖርያ ቤቶችን ፤ እንዲሁም በአካባቢው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ የሸራ ሱቆች የንግድ ስራ ሲሰሩ የነበሩትን የንግድ ቤቶች ዘመናዊ በሆኑ 28 የንግድ ሱቆች በመቀየር ፤ የሸገር ዳቦና የአትክልት መሸጫ ሱቅም አብሮ ለምረቃ በቅቷል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ከአካባቢው ሞዴል የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ ጋር እንዲያያዝ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ የምገባ ማእከሉ የአትክልት ምርቶችን እዛው እንዲያገኝ ለማድረግ የታሰበም ጭምር ነው፡፡
የምገባ ማዕከሉ ለ60 እናቶችና ለ12 የጥበቃ ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድልን የሚፈጥር ሲሆን ግንባታው በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አማካኝነት የተከናወነ መሆኑም ተገልጧል፡፡
በዚህ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች እንደተናገሩት ዛሬ የምገባ ማእከል ቤትና ሱቅ ብቻ ሳይሆን ያበረከትነው ለእናንተ ያለንን ክብርና ፍቅር ያሳየንበት ስራ ነው ብለዋል፡፡
ይሄ ደግሞ መጀመርያ የተሰራው ጭንቅላት ውስጥ ነው፤ በሃሳብ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ፤ ገና በለውጡ ማግስት ወደ አመራር ስንመጣ፤ የምንከተለው የፖለቲካ እሳቤ ሰው ተኮር ነው ስንል፤ ለሰው ልጅ ተገቢውን ክብር ካልሰጠን ፕሮጀክት ብንገነባም አንድ ቀን መፍረሱ አይቀርም፤ ሰው ላይ የሚሰራ ስራ ግን ከትውልድ ትውልድ ይሻገራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከተረጂነት አንፃርም አንዳንዶች እንደሚሉት ሳይሆን ስራ እድል ልንፈጥር የምንችለው የዛሬን ጫና አቃለን ነው ያሉ ሲሆን ይህ ደግሞ ከራስ በላይ መኖር ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከጀመርነው ፕሮጀክት ሁሉ አስደስቶኛል ያሉት ከንቲባዋ እዚህ ቦታ ስንመጣ ይዘናቸው የመጣናቸው ባለሃብቶች ሰፈሩ ያስቸግራል በማለት ለመግባት ፈርተው ነበር ፡፡ እኛ የፈራነው ማን ይለውጠዋል፤ ጠጋ ብለን እንያቸው ፤ ብለን ስንገባ ራሳቸው ናቸው ያፀዱት፤ ውስጣቸው መስራት መለወጥ እንደሚፈልጉ ተመልክተናል፡፡
አንዳንዶች ግን የአዲስ አበባን ህዝብ እንወደዋለን በሚል እሳቤ በፌስቡክ በዩትዩብ ቃላት ስንጠቃ ለአዲስ አበባ ህዝብ ፍቅራቸውን ያሳዩት ይመስላቸዋል፡፡ ህዝቡንም ሊያጭበረብሩት ይሞክራሉ ያሉት ከንቲባዋ የአዲስ አበባን ህዝብ መውደዳችንን የምናረጋግጠው በወሬ አይደለም፡፡ ተስፋውን ሊያለመልም የሚያስችል እንደዚህ አይነት ስራ በመስራት ነው ብለዋል፡፡
እንደዚህ ለመስራትም የግድ ባለስልጣን ወይንም ባለሃብት መሆን አይጠበቅም ያሉት ከንቲባ አዳነች ባለስልጣንም ባለሃብት ያልሆኑ አስተባብረው ጎረቤቶቻቸውን ሲረዱ አይተናል፡፡
ትክክለኛ ለውጥ የምንፈልግ ከሆነ መተሳሰብን በተግባር እያሳየን ነው መሆን ያለበት፡፡ የምንችለውን ያህል ከሰራን እንለወጣለን፡፡11 አመት የፈጀ ፕሮጀክት ባለበት ቦታ እዛው በ2 ወር ተመሳሳይ ህንፃ መጨረስ መቻላችንን በዚህ ከተማ አሳይተናል ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡