የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የህዝቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እንሰራለን፣ ሰርተንም እናስረክባለን” ሲሉ ተናገሩ።
በቂርቆስ ክ/ከተማ እየተገነቡ ያሉ የ60 ቀናት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ጎበኝተዋል።
ከዚህ በፊት በርካታ ሰው ተኮር የሆኑ ተግባራት በክፍለ ከተማው በፍጥነት ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉ ይታወቃል።
የህዝብ አገልግሎት ዘርፎች፣ የከተማ ማስዋብና የከተማ ግብርና ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
በጉብኝታቸውም አብዛኞቹ ስራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ሌሊትና ቀን ያለ ዕረፍት ሰርተን ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግወደ ሌላ ሰው ተኮር ተግባራት እንሸጋገራለን ብለዋል።
ግንባታዎችም ሆኑ ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውም ችግሮች ካሉ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የሚፈቱበትን አግባብ ለማመቻቸት በተለየ ሁኔታ እየሰራ ነው።
እስካሁን ባለው ሂደትም ለበርካታ ችግሮችና የአሰራር ማነቆዎች መፍትሔ እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከፕሮጀክት ጉብኝቱ ጎን ለጎንም በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያለውን የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በአገልግሎቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በወረዳዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አገልግሎት ፈልገው ከመጡ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ውይይት በማካሄድ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ዘመናዊ አስራር ለመዘርጋት ከተማ አስተዳደሩ ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።