የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን የመኖርያ ቤት ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራጭ እቅዶችን በመንደፍ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡
ከነዚህም መሃከል በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የ10ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ ሞዳሊቲ አንዱ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት በቦታው ላይ አጋጥሞ በነበረ የፍርድ ቤት እግድ ምክንያት ተቋርጦ የነበረና አሁን ግን በከፍተኛ ፍጥነት ግንባታው እየቀጠለ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡
ከንቲባዋም በቦታው ተገኝተው ግንባታው ስላለበት ሁኔታ የመስክ ምልከታ በማድረግ ግንባታው ስለሚፋጠንበት ሁኔታ የስራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘውም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዮናስ አያሌውም በበኩላቸው የተጀመሩትን ግንባታዎች ድርጅታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ገልፀው አዳዲስ ብሎኮችንም በቅርቡ ውስጥ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት የቤት ልማት ስራ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን ማስቀመጡን አውስተው የቤት ፈላጊዎችና የግል ባለሃብቶች በነዚህ አማራጮች በመጠቀም በቤት ልማት ላይ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡