ዋናው የውይይቱ አላማ ህዝብን ማዳመጥ ነው፡፡

ህዝቡ በየመድረኩ የተሰሩትን መልካም ስራዎች እያመሰገነ ፤ትክክል ነው ተሰርተዋል፤ አገልግሎት ሰጥተውናል፤ ነገር ግን ይቀራል ያላቸውን አንድ ሁለት ሶስት ብሎ ቆጥሮ ያነሳቸው ጉዳዮች ጉባኤያችን ካያቸው ጋራ የሚጣጣሙ ናቸው፡፡

በዚህ ህዝብ ውይይት እንደተለመደው አይነት የተሳታፊ ግብዣ አይደለም ፤ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ፤ የመረጠንም ያልመረጠንም ወደ ስብሰባው መጥቶ እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡

በዚህ ስብሰባ ህዝብ በነፃነት መናገር ችሏል፡፡ በአንድ ጊዜ መላ የኢትዮጵያ አካባቢ ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር ህዝቡ ተናግሯል፡፡

ህዝቡ አስተያቶችን አቅርቧል ፤ ትችቶችን ሰንዝሯል፤ ጥያቄዎችን ጠይቋል፤ የመፍትሄ ሃሳብም አስቀምጧል፡፡
ይህ በአንድ በኩል ፓርቲው ላይ ያለውን መተማመን ያሳያል፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ችግሮቹን ይፈታል ብሎ ባያምን ኖሮ እንደዚህ ነው ብሎ ወደ ስብሰባም ባልመጣ ነበር፤አዳራሽ ጠቦ ሰው እስኪመለስ ደርሷል፡፡

ፓርቲውም ህዝቡ በሚዛናዊነት ጥያቄ ሊያነሳ እንደሚችል እምነት ነበረው፡፡ ይሄንንም ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ህዝቡ ያነሳቸውን በሶስት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡
1. በአብዛኛው ያነሳው እውነት የሆነ ፤መደረግ ያለበት ሊደረግም ሊፈፀምም የሚገባው ነው፡፡
2. በሁለተኛ ደረጃ በግንዛቤ ክፍተት የሚነሱ እንዳሉም አይተናል፤ እሱም የኛ ችግር ነው፡፡ ማስገንዘብ ስላለብን፤ ስራዎቻችንን ግልፅ ማድረግ አለብን፡፡
3. ሚዛናዊ ያልሆኑ አንዳንድ የተሰሙ ድምፆች አሉ፡፡ ሆኖም እነርሱም ቢሆኑ እንኳን ተነፈሱ ነው ያልነው ፡፡ በጨዋነት እስከሆነ ድረስ ችግር የለውም፡፡ ህዝቡ ራሱ የትኛው ትክክል የትኛው ትክክል አይደለም የሚለውን መለየት ይችላል፡፡

ህዝብን ማዳመጥ ያስተምራል፤ ከህዝብ ጋራ ከተነጋገርንና ከተወያየን ችግሮችን መቅረፍ እንደምንችል አይተንበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም የበለጠ የተረዳንበት ነው፡፡ ከህዝብ ጋራ ካልሰራን በስተቀር ህዝቡ ካላገዘን በስተቀር፤ ሁሉንም ችግር በመንግስት አቅም ብቻ ሊቀረፍ እንደማይችል የተማርንበት ነው፡፡

ህዝብ በጥያቄ ያነሳቸው፡፡
1. በመላ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ይከበር ነው የመጀመርያው ጥያቄ
2. የኑሮ ውድነት ነው ፤
3. ሌብነት ነው፡፡ ህዝቡም በግልፅ ቋንቋ ነግሮናል ይሄንን ፤በውስጣችሁ ያለውን ሌብነት ተቆጣጠሩ ፤አትስረቁ ፤አተታሰርቁ ግልፅ ሆነ መልእክት አስተላልፏል፡፡
4. ህዝቡም ያነሳው እኛም ያነሳነው አክራሪነትና ፅንፈኝነት ኢትዮጵያን ያፈርሳታል የሚለው ነው፡፡

ህዝቡ ኢትዮጵያዊ አንድነቴ በመከባበር በመተባበር ይገንባልኝ ነው ፡፡ ጥያቄዎቹ ተመሳሳይ ፤የተሳሰሩና በጋራ የሚፈቱ ናቸው፡

በዚህ በብልፅግና ጉባኤ ያረጋገጥነው ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆምን የማንፈታው ችግር አለመኖሩን ነው፡፡

መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት ቁርጠኝነት ስላለው ነው ወደ ህዝብ የወረደው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር በአንዴ አይፈታም፡፡ ቅድመ ተከተል ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ለህዝብ ግልፅ መደረግ አለበት፡፡ የትኞቹን ነው በቅርብ ጊዜ መፍታት የምንችለው ፤ጊዜ የሚወስዱ ደግሞ የትኞቹ ናቸው ፤ጊዜ የምንለውስ እስከመቼ ነው በሚገባ ለይተን ከህዝቡ ጋር እንነጋገራለን።

የህግ በላይነት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡

ሁሉም ነገር በመንግስት ብቻ ስለማይሰራ ፤ ወደ ህዝባችን ቀጣይ ምክክር ሂደት እንገባለን፤ ሰፊ ቁጥር ባይሆንም፤ እንደየወረዳውና ክ/ከተማው ህዝቡም መደገፍ ያለበትን እየደገፈን በዛው ልክ ደግሞ ማጋለጥ ያለበትንም ፤ለኛ ማደረስ ያለበትን መረጃዎች እንዲያደርስ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ፤የህዝባችንን እገዛ ዋና ተገንና ጉልበታችን አድርገን ወደ መፈፀም እንገባለን!!