በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ ያለው የከተሞች የተቀናጀ የጓሮ አትክልት ልማት እንቅስቃሴ በተለያዮ መንግስታዊና የግል ተቋማት እየተተገበረ ሲሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት በከተማው የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በመስክ ምልከታው ወቅት እንደተናገሩት የከተማ ግብርና፤ በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ተሰጥቶት በግለሰቦች መኖሪያ ግቢ፣በመንግሥት ተቋማት በሚገኝ ክፍት ቦታና መሠል ክፍት መሬት በተገኘበት ሥፍራ ሁሉ በንቅናቄ መልክ ተጀምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በመደጎምና ትኩስ የአትክልት ውጤቶችን ለተጠቃሚ በማድረስ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን በየአካባቢው ተዟዙረን እየተመለከትን ነው ብለዋል ።
ዛሬ በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተመለከትነው የግብርና ሥራ በአጭር ግዜ፣ በጠባብ መሬት ላይ የተቀናጀ የከታማ ግብርናን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ማስረጃ የሚሆነን ነው ያሉት ከንቲባዋ በዚህ ጠባብ ቦታ የንብ ማነብ ሥራ፣ የአሳ እርባታና ሌሎችም በአጭር ግዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የጓሮ አትክልቶችን ማልማት መቻሉ ለሁሉም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
ይህ ለሌሎችም ማድረግ እንደሚቻል ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆን ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በተለይ ለዝቅተኛ ገቢ ማህበረሰብ የኑሮ እፎይታን መፍጠር የሚቻል በመሆኑ ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።