በመላው ሀገራችን የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሃይል አስታውቋል፡።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሃይሉ ቅደመ ዝግጅት በማድረግ የአዝማሚያ ትንተና በማካሄድ ተጋላጭ ቦታዎችንና አካባቢዎችን ለይቶ በቅድመ መከላከል ስራው ላይ በርካታ የሰው ኃይል አሰማርቶ ከህዝቡ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባቶችና ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን ያስታውቃል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው ህዝባችን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀይማኖት አባቶች፣ ለበዓሉ አስተባሪ ኮሚቴዎች እና ለወጣቶች ግብረ ሃይሉ ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።
የፀጥታና ደህንነት ሃይሎችም ከህብረተሰቡና የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር በመቀናጀት የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ ስለተወጡ ግብረሃይሉ ላቅ ያለ ምስጋናውን አቀርቧል፡፡
የሀገራችን ጠላቶችና እነርሱ የሚመራቿው አሸባሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በደህንነታችን ላይ አደጋ ለማድረስ ስለሚጥሩ ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር ወደፊት በሚከበሩ ሌሎች ህዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላት ላይም አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሃይሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡