የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በእድገት ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ለምርምርና ለአስተዳደር ቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ባለ ሁለት ፎቅ የህንፃ ግንባታ የመሠረት ድጋይ አስቀመጠ።
የህንፃው ግንባታ ሙሉ ለሙሉ በቲ ኤን ቲ ኮንስትራክሽንና ንግድ ስራዎች ድርጅት የሚሸፈን ሲሆን ቤተ-መፅሐፍት፣ላብራቶሪ፣የአይ ቲ እና የአስተዳደር አገልግሎት መስጫ ቢሮችን ያካተት እንደሚሆን በስነስርአቱ ላይ ሲገለፅ አጠቃላይ ግንባታውን ጀምሮ ለማጠናቀቅ ከ41ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይፈጃል ተብሎም ይታሰባል።
በዚህ የግንባታ የመሠረተ ድጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላት በስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የትምህርት ስራ የመምህራን ወይንም የአንድ አካል ኃላፊነት ብቻ አይደለም ስለሆነም ትምህርት ተቋማት ትውልድ የሚፈልቅበት፣ትውልድ የሚፈራበትና የሚገነባበት ነው።ስለዚህ ሀሳብ የሚታነፅበት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጥላሁን ሮባ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲህ አይነት ተማሪዎችን ለምርምርና አዲስ ነገር ለመፍጠር የሚያግዙ እንዲሁም የአስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ግንባታዎች መደረጋቸው በዘርፉ እጅጉን አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ይህን ግንባታው ለማከናወን ተግባሩን በሙሉ ፍቃደኝነት ወስዱ ስራውን ለመስራት ቲ ኤን ቲ ላሳያው ቁርጠኝነት በአስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውንም ቸረዋል።
የቲ ኤን ቲ ኮንስትራክሽን እና የንግድ ስራዎች ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጂነር ተስፋዬ ጥላሁን ድርጅታቸው እንዲህ አይነት መሠል ስራዎች በሌሎች ክፍለ ከተሞች እየሠሩ መሆኑን ገልፀው በዚህ በታሪክ ማህደር በሚቀመጥ የትውልድ ግንባታ ላይ አሻራቸውን በማኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል።