ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በከተማዋ በሚስተዋሉ የኑሮ ውድነት ምክንያቶችና መፍትሄዎች ዙሪያ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተወያይተዋል ።
በኢኮኖሚው ላይ አሻጥር የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርና ሕዝብ እንዲማረር የሚያደርጉ ጫናዎች እየተፈጠሩ መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የንግዱ ማኅበረሰብ ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ከትርፍ ይልቅ ሀገርን እና ሕዝብን ማስቀደም እንዳለበት ጠቁመዋል ።
ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር ፣ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና በመሳሰሉት ህገወጥ ተግባራት የሚሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ ስግብግብ ነጋዴዎችን መቆጣጠር እና አሳልፎ መስጠት እንደሚገባ ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል ።
ለዚህም የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመፍጠር ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ሰዉ ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት በሚፈጥሩ አካላትን የሚከታተል እና የሚቆጣጠር ግብረሃይል መዋቅሩን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።
በውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ሕግና ሥርዓትን አክብረው የሚሰሩ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን ምክንያት በማድረግ ገበያውን በሞኖፖሊ መያዝ ፣ምርቶችን በመደበቅ ባልተገባ መንገድ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸውን አመልክተዋል ።
ምርት በማሸሽ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና የንግድ ሰንሰለቱን በማርዘም የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ አብዱፈታህ ጠቁመዋል ።
ከሁሉም ክፍለከተሞች የተውጣጡ አስመጪና ላኪዎች ፣አከፋፋዮች እና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የውይይት መድረክ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።