በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ መሰረት በመጪዎቹ የበአል ቀናት ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን የጀግና አቀባበል ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነዉ።
የአዲስአበባ ባህል ኪነጥብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሂሩት ካሳዉ በአቀባበሉ በባህል ቱሪዝም ዘርፍ እየተሰራ ያለዉን የቅድመ ዝግጅት ስራ አስመልክቶ ለሚዲያ ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸዉ በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን እዉነት ለአለም በማሳወቅና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በመቀልበስ፤ የበቃ ዘመቻን በመቀላቀልና ዉጤታማ ስራ በመስራት የህልውና ዘመቻ ግንባሩን በድል የተወጡ ዳያስፖራ ጀግኖቻችንን ስንቀበል የከተማው ነዋሪ ለነዚህ ጀግኖች የአገር ልጆች አክብሮት በመስጠትና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።
ለዚህም በመጪዎቹ የበአል ቀናት ወደ አገርቤት ለሚመጡ ከ 1ሚሊዮን በላይ ዳያስፖራዎች አቀባበል ከቦሌ አለምአቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ አንስቶ ፤ በሆቴሎች ፤ በትራንስፖርት አቅራቢዎች ፤ በጉብኝት ስፍራዎች ለዚህ ክብረበዓል በተለየ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ፤ የእንግዳ ማረፊያዎች ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች እስከ 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም በመግለጫው ተናግረዋል ።
አያይዘዉም ወደ አገርቤት እንደሚመጣ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ቁጥር አንፃር የሆቴሎች የመኝታ አቅርቦት አለመመጣጠን ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ የእንግዳ ማረፊያ ፤ አፓርትመንት ያላቸው ግለሰቦች በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ተቋም በመሄድ ጀግኖች እንግዶቻችንን በተገቢ መንገድ ማስተናገድ እንዲቻል ተገቢና ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ በመተመን እንዲያሳዉቁና ለመኝታ አገልግሎት ምቹ የማድረግ ስራ ከወዲሁ እንዲጀምሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።