” በዘመቻ በትምህርት ልማት ግምባር” ተሳታፊ የነበራችሁ
የከተማችን ተማሪዎች ፣መምህራንና የትምህርቱ ማህበረሰብ አካላት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ” ከንቲባ አዳነች አቤቤ.
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “በዘመቻ በትምህርት ልማት ግምባር” ተሳታፊ ለነበሩ ከ 30ሺህ በላይ የአዲስአበባ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ፤ መምህራንና የትምህርቱ ማህበረሰብ አካላት ምስጋና አቀረቡ።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገፃቸዉ ላይ ባሰፈሩት የምስጋና መልዕክት ዘመቻ በትምህርት ልማት ግምባር ይዞት ከተነሳዉ ግብ አንፃር በድል ተጠናቋል ያሉ ሲሆን ተማሪዎች ፣ መምህራንና አጠቃላይ የትምህርቱ ማህበረሰብ ላሳዩት ከፍተኛ የአገር ፍቅር የታየበት አፈጻጸም አመስግነዋል፤ አያይዘውም በዘመቻዉ ተካፋይ የነበሩ ተማሪዎች መምህራንና እና አጠቃላይ የትምህርቱ ማህበረሰብ ወደ መማር ማስተማር ተግባሩ መመለሳቸውን ይፋ አድርገዋል ።
በዚህ የልማት ዘመቻ ማህበራዊ አገልግሎት ስትሰጡ የነበራችሁ የከተማችን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ መምህራንና አጠቃላይ የትምህርቱ ማህበረሰብ አካላት የዘማች አርሶአደርና ሚሊሻዎችን ቤተሰቦች የደረሰ የመኸር ሰብል በመሰብሰብ፣ ደም በመለገስ፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ለነበራችሁ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት የታየበት ተሳትፎ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በበጎ ስራችሁ ተደራሽ ባደረጋቹሀቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ስም እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ ብለዋል ።