የከተማው አስተዳደር ከሚያሰራቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ መካከል በትራንስፖርት ዘርፍ ምቹ፣ ቀልጣፋና በርከት ያሉ ተቋማት አገልግሎትን በአንድ ቦታ መስጠት ያስችላል ተብሎ የታመነበት፤ የትራንስፖርት ዘርፍ ዋና መሥሪያ ቤት የፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀም 51 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
የፕሮጀክቱ ተወካይ መሃንዲስ ታደለ ዳንደና(ኢንጂነር) እንደገለፁት፤ የከተማው አስተዳደር ለህንፃ ኪራይ የሚያወጣውን ወጪ በመቀነስ እንዲሁም የተገልጋይን ጊዜና ወጪ በመቀነስ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ከመስጠት አንፃር የፕሮጀክት ግንባታው ፋይዳ የጎላ እንደመሆኑ፤ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ በመሆኑ፤ አሁን ላይ አፈፃፀሙ 51 በመቶ ላይ ደርሷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አክለውም ፕሮጀክቱ በየደረጃው ካለ የበላይ አመራር ጀምሮ ልዩ ድጋፍና ክትትል ተደርጎለት እየተሰራ ያለ የከተማው አስተዳደር ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡
የፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ ለህዝብ ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ ለአሽከርካሪዎች እና የተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ማረጋገጫ ባለስልጣን፣ ለትራፊክ አስተዳደር ባለስልጣን፣ ለአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ እና ለትራንስፖርት ፕሮግራም አስተዳደር ቢሮ አገልግሎት ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡