የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን 1 ሺህ 496ኛውን የመውሊድ በዓል ምክንያት በማድረግ በወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን በመገኘት ማዕድ አጋርተዋል ።
በመርሃ ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደገለጹት ወንድም ካሊድ የወገኖቹን ህይወት ለመቀየር እያከናወነ ያለው በጎ ተግባር በእጅጉ የሚመሰገን ነው ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው አቅም ወገኖቹን ቢረዳ መልካም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይም በጎዳና የሚገኙ ወገኖችን የማንሳትና የመርዳት ራዕይ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከወንድም ካሊድ በጎ ምግባር ሁሉም ሊማር ይገባልም ፤
ሁሉም ዜጋ ወገኖቹን የመርዳት ድርሻ አለው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይ በበዓላት ወቅት ወገኖችን ማስታወስና መርዳት ሊለመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
“ዛሬ እያንዳንዳችን የምናደረገው ጠብታ ነገ ትልቂቷን ኢትዮጵያ እንድንገነባ ይረዳናል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ከ 1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ከጎዳና በማንሳት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል ።