ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ክብር ለመስጠት በከተማዋ ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዟል፡፡
“ኑ ኢትዮጵያን እናልብስ” በሚል ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እና የኢፌድሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጀነራሎች እና የሰራዊቱ አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳስታወቁት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ልዑአላዊነት በማስጠበቅና አንድነቷ ተጠብቆ እንድትቆይ ደሙን ሰጥቶ መስዋዕት ሆኖ እዚህ ስላደረሰ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር በማስጠበቅ፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ከሚከፍለው መስዋዕትነት ባለፈ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ለሚያደርገው ተሳትፎ ሊመሰገን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ከተማ አስተዳደሩም 500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ጥራቱ ተናግረዋል።
የመከላከያ ኢንዶክትሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል አስፋው ማመጫ ሰራዊቱ የሀገር ዳን ድንበር ከመጠበቅ እና ከማስከበር ስራዎች በተጓዳኝ ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት ለማሳየት በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጆች ሁሉ በስኬት እንዲፈጽም የህዝቡ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ብርጋዴር ጀነራል አስፋው የከተማዋ ነዋሪዎች በህግ ማስከበርም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች እያሳየው ባለው ድጋፍና አብሮነት ለሰራዊቱ የሞራል ስንቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው መሳሪያ በመታጠቁ ሳይሆን ከህዝብ ጋር ልማት ስለሚሰራ እንደሆነ የተናገሩት ብርጋዴር ጀነራል አስፋው የዛሬው ችግኝ ተከላ መርሐግብርም የሰራዊቱ የልማት ተምሳሌትነት እንደሆነ ተናግረዋል።
ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ክብር ለመስጠት እና በግዳጅ ላይ እያሉ ለተሰዉ የሰራዊቱ አባላትን ለማስታወስ በተከታታይ 10 ቀናት ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱንና የዛሬው ችግኝ ተከላ መርሐግብርም የዚህ እቅድ አካል መሆኑን በመርሐግብሩ ተገልፆል፡፡