አዲስ አበባችን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ብርሃን ትሆናለች ብለን ስንነሳ፤ ከተማዋን ውብና ዘመናዊ ከማድረግም ባሻገር በአስተሳሰቡ ያደገ እና የላቀ ትውልድ ፤ የቆየውን የህዝቦች ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚያስቀጥል፤ በጠንካራ ህዝቦች አንድነት ላይ የተመሰረተ የእድገትና ብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ማለታችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ትንሳኤ መሰረቱ የህዝቦች አንድነት በመሆኑ በህብረብሄራዊነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የህዝቦች አንድነትንና አብሮነትን ማጠናከር ደግሞ የሁሉም ሃላፊነት የሚሰማው ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ቀዳሚ ሚና መሆን አለበት፡፡
መገንባት የብልሆችና የአስተዋዮች ሚና ነው፤ ማፍረስ የደካሞችና የተሸናፊዎች ተግባር ነው፡፡ መገንባት ከማፍረስ ይልቅ ከባዱ ስራ ነው፡፡ መገንባት እውቀት ፤አርቆ አስተዋይነት ሆደ ሰፊነት ፤እና ልበሙሉነት ትእግስት ይጠይቃል፤ ለማፍረስ እነኚህ ሁሉ አያስፈልጉም፡፡ አሉታዊ ግፊት ብቻውን በቂ ነው፡፡
ይህች ውድ አገራችን ከጥንት ቅድም አያቶቻችን ጀምሮ በብዙ እጀ ውብ አናፂያን ጥበብ ታንፃና ተገንብታ እኛ እጅ ላይ ደርሳለች፡፡
በዚህ ሂደት ብዙ እውቀት ፤አስተዋይነትና ሆደ ሰፊነት ነበሩበት ፤ የአባቶች ፀሎትና ምልጃ የአዋቂዎች ምክርና ግሳፄም የኢትዮጵያ አሻራ መልኮች ናቸው፤ አባቶቻችን ዛሬን አሻግረው ባያስቡ ፤ በአካባቢ አጀንዳዎችና በከፋፋይ ትርክቶች ቢታወሩ ኖሮ ምናልባትም እቺን ሃገር ከነክብሯና ሞገስዋ ባላገኘናት ነበር፡፡
የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ደግሞ እጁ ላይ የገባቸውን ውድ ሃገር ይበልጥ አሳምሮ የነበረውን ጠብቆ የህዝቦች አብሮነቷና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀች ነፃ ሃገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡
ስለሆነም አብሮነታችን ቀዳሚ ፍላጎችን ብቻ ሳይሆን የትውልዱ የግንባታ ማእከል ጭምር በመሆን ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚበጁ ጡቦችን በማቀበል እንጂ የተገነባውን በማፍረስ በኢትጵያ ድካም እና ውድቀት ላይ ለማትረፍ መሯሯጥ አይበጀንምና ስለሁሉም ነገር ቆም ብለን ብናስብ ይበጃል እንላለን!!
አንድነታችን እንዲጠናከር እኔ በግሌ ምን እያደግኩ ነው??
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!