በዛሬው እለት ለከተማ አስተዳደሩ የተበረከቱትን ለጓሮ አትክልትና የከተማ ግብርና ስራ የሚውሉ 200 የውሃ ፓምፖችን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ እጅ ተረክበዋል።
በርክክብ ስነስርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ወንዞችን በማከምና ፓምፖችን በመጠቀም ብዙ ምርት ማምረት እንደምንችል አጥንተናል ያሉ ሲሆን ዛሬ የተደረገልን ድጋፍ ለዚህ አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ ለከተማው እና በዙሪያዋ ላለው ገበሬ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰው የሌማት ትሩፋት ብለን እንደ ሀገር ይፋ አድርገን እንደከተማችንም ወደስራ ገብተናል ብለዋል።
መመገብ መቻል ከመስራት ይገኛል፤ መራብ የለብንም፤ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ አለብን ከዛም ተርፈን ወደ ውጪ የምንልክ ዜጎች መሆን አለብንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነር አይሻ አህመድ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር በበኩላቸው በከተማ ውስጥ የመስኖ ስራ እየተስፋፋ ስለሚገኝ ይህንን ስራ እንደ ሚኒስቴር መስርያ ቤት ልንደግፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህንን የማስፋፋት የከተማ አስተዳደሩ ስራ ብቻ አይደለም፡፡ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ተቋማትና ድርጅቶችም ይህንን ተግባር ማገዝ እንዳባቸው አሳስበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በርክክቡ የከተማውን ሕዝብ ኑሮ ለመቀየር የሚኒስቴ መስሪያ ቤቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ” ይሕንን የሰጣችሁንን ድጋፍ በትክክል ለሚገባው አካል አድርሰን ውጤቱን አብረን የምንጎበኘውና የምናየው ምርቱንም በጋራ የምንጠቀምበት እንደሚሆን ቃል ልገባ እወዳለሁ”ብለዋል።