ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን የኑሮ ውድነት እየተባባሰ እንደመጣ የሚታወቅ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በአብዛኛው አሳማኝ እና ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው በሰውሰራሽ ምክንያቶች የተፈጠረ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱም የከተማችንን ነዋሪ ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል፡፡
በሰሜን የሃገራችን ክፍል ሃገር በማፍረስ ተግባር ላይ የሚገኘውን የአሸባሪው ህወሃት እንቅስቃሴ ለማክሸፍ እየተደረገ ካለው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የከተማችን ነዋሪ በገንዘብ መዋጮ፤ ለሠራዊት የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀት፤ ደም ልገሳ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ባለበት በዚህ ወቅት ጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች በተቃራኒው ቆመው ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ፍፁም ባፈነገጠ መልኩ አሁን ካለው ችግር ላይ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የተለያዩ ተግባራት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡
መንግሥት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከውጭና ከውስጥ ያሉ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሀገር የማፍረስ ተግባር እንዲከሽፍና የዜጎች የኑሮ ጫና እንዲቀንስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም መሠረት እስከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍልን የሚያሳትፍ የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቀልበስ የተቋቋመው ግብረይል በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥም ግብረሃይሉ ባካናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ባሻገር አለግባብና የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የቤት ኪራይ ጭማሪ የነዋሪውን ሕይወት በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል፡፡
ይህም ወቅታዊ ሁኔታን በመጠቀም አላግብ ለመክበር የሚደረግ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መተሳሰብ ጋር በፍፁም የሚቃረን ተግባር ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም የኮቪድ 19 ወረርሽ በሀገራችን መገኘቱ ተከትሎ በርካቶች ችግር ውስጥ በገቡበት ወቅት የከተማችን ነዋሪዎች እርስ በእርስ ከመረዳዳትና ማዕድ ከመጋራት አልፎ በርካታ ቤት አከራዮች የወራት የቤት ኪራይ ዋጋ ለተከራይ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀንሰው ችግሩን በጋራ ለመፍታት ኢትዮጵያው የመረዳዳት እሴታችን የታየበት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህም በወቅቱ በሕግ ተቀምጦ የነበረውን የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የሚከለክለውን ድንጋጌ ሳይጨምር ነው፡፡
አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በቤት ክራይ ላይ ዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡
ስለሆነም አሁን እየታየ ያለውን አላግባብ የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብ የነዋሪውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቀን 18/12/13 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ በቀረበ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡
በዚህም መሠረት ደንቡ ከፀደቀበት 18/12/13 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ ሲሆን በቀጣይም ታይቶ ለተጨማሪ ቀናት ክልከላው ሊራዘም ይችላል፡፡
ደንቡን በመተላለፍ ጭማሪ የተደረገበት ተከራይ አቤቱታውን በፅሑፍ ለወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት በማቅረብ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚቻልበት ሥርዓት በደንቡ ተደንግጓል፡፡
በዚሀ መሰረት በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ባደረገ አካል ላይ በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ምንም እንኳን ይህ ደንብ የወጣው ዜጎችን ካላስፈላጊ ጫና ለመከላከልና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ቢሆንም ህብረተሰባችን በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ችግሮችን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ለማለፍ ያሳየውን ኢትዮጵያዊ የጨዋነትና አብሮነት እሴቶቹን በማዳበር ይህን ወሳኝና አስቸጋሪ ጊዜ በጋራ ማለፍን ማዕከል በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ነሐሴ 22 ቀን 2013
አዲስ አበባ፤