አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014፤ የመገናኛና አንዋር መስጊድ አካባቢ ስማርት የመኪና ማቆሚያዎች ጥገና ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
መገናኛ ስማርት የመኪና ማቆሚያ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ በኤሌክትሪካል ቴክኒክ ችግር ምክንያት ተቆርጦ የነበረ ሲሆን፥ በተመሳሳይ አንዋር መስኪድ አካባቢ የተነባው ስማርት የመኪና ማቆሚያ የኤሌክትሪክ መስመሩ በመቆረጡ አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሁለቱም ስማርት የመኪና ማቆሚያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ ለስማርት የመኪና ማቆሚያዎች ጥገና እንደተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሙሉ አቅማቸው የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለኦፕሬተሮች ስልጠና እንደሚሰጥ አቶ አካሉ ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ስማርት የመኪና ማቆሚያ 90 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ባለ 15 ደረጃ ያለው ሲሆን፥ ከአጠገቡ 105 መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያ አለው፡፡
በተመሳሳይ በአንዋር መስጊድ አካባቢ ለ80 መኪናዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል፤ በመሬት ላይ ደግሞ 110 መኪናዎችን የመያዝ አቅም አለው፡፡
በመገናኛና አንዋር መስጊድ አካባቢ የተገነቡ የስማርትና የመሬት ላይ የመኪና ማቆሚያዎቹ ለመዲናዋ ብሎም ለሀገሪቱ አዲስና በዓይነታቸው የመጀመሪያ የሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ ናቸው፡፡
የመኪና ማቆሚያዎቹ የከተማዋን የትራንስፖርት ስርዓት ለማዛመን ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በመዲናዋ አዲስ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ታስበው የተገነቡ ናቸው፡፡