የማልማት ጥያቄ አቅርበው ፕሮጀክቶቻቸው ለከተማዋ ዕድገት ካላቸው የላቀ ፋይዳ እና ከሚፈቱት የህዝብ ችግር አኳያ መሬት በምደባ ከወሰንንላቸው ባለሀብቶች እና የዕምነት አባቶች ጋር ዛሬ ተወያይተናል፡፡
150 ሔክታር መሬት በምደባ ለመስጠት የወሰንነው ያቀረቧቸው ፕሮጀክቶች የከተማዋን ታላቅነት የሚመጥኑ፣ ለከተማው ነዋሪ ከሚፈጥሩት የስራ ዕድል፣ ለከተማዋ ዕድገት ከሚያበረክቱት የላቀ አስተዋጽዖ እንዲሁም ከሚያቃልሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አኳያ ፈትሸን በመሆኑ በታማኝነት እንደሚያለሙት ተግባብተናል፡፡
በግልጽ አሰራር ባለሀብቶቹ ያቀረቡትን ፕሮፖዛል ፈትሸን በምደባ ለመስጠት የሰወንነው ከተማችንን የሚመጥኑ ግዙፍ እና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ ሞሎችና ሆቴሎች እንዲገነቡ ፣ የከተማው ነዋሪ የስራ ዕድል እንዲፈጠርለትና የከተማዋ ገቢ እንዲጨምር ለማድረግ በመሆኑ ባለሀብቱ በዚህ የከተማዋ ፍላጎት ልክ መዘጋጀትና ማልማት የሚጠበቅበት መሆኑን በጥብቅ አሳስበናል፡፡
በውይይታችን መሬት የወሰንንላቸው አልሚዎች በዚህ ልክ ግልጽነትና ፍትሃዊነት የነገሰበት አሰራር ተበጅቶ አልሚዎች ሆቴሎችና ሞሎች፣ የዕምነት ተቋማት ደግሞ የማምለኪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉ ፍትሀዊነትና ዕኩልነት በተግባር ያሳየ በመሆኑ ለከተማ አስተዳደራችን ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በታማኘነት መሬቱን ለታለመለት ዓላማ በማዋል፣ መንግስት የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ ታላቅ ፕሮክቶች በመገንባት እያደረገ ያለውን ስራ በተግባር በማገዝ፣ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠውልናል፡፡
መሬት በምደባ የሰጠናቸው አልሚዎች እና የዕምነት ተቋማት ማነቆዎች እንዳያጋጥሟቸው በከተማ ደረጃ ድጋፍ የሚያደርግ አንድ ቡድን ተቋቁሞ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡
ለከተማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና አሻራችንን በጋራ እናኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ