የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብር ተግባራዊ መሆን በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በዘንድሮው ትምህርት ዘመን ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመያዝ በሁሉም የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ምገባ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም ገልጿል።
በእያንዳንዱ ምርት ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ 80 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ጨምሮ አስታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢሳያስ ምህረት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመርሃ ግብሩ ተግባራዊ መሆን ወላጆች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ መተማመን እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር መጠነ መቋረጥ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።
በዚህም በ2013 የመርሃ ግብሩ አተገባበር ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ከ240 በላይ ተጨማሪ የመመገቢያና የማብሰያ አዳራሽ ተገንብተዋል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ለሚሳተፉ 10 ሺህ እናቶች የኮቪድ-19 ክትባት እንደተሰጣቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የምገባ መርሃ-ግብሩ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ40 ሺህ በላይ ተጨማሪ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማድረጉንም የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የምገባ መርሃ-ግብሩ ጥቅም 1 ቀን 2014 እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።
የተማሪዎች የደንምብ ልብስ ትምህርት በተጀመረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተሰራጭቶ እንደሚጠናቀቅ ጠwቅሰው፤ እስካሁን ባለው ጊዜ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደብተር ለተማሪዎች መሰጠቱን ተናግረዋል። የደብተር አቅርቦቱ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የምገባ መርሃ-ግብሩ የወላጆችን ጫና ከማቃለሉ ባሻገር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉ በማድረግ ለሀገር ግንባታ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ተማሪዎች መንግስት የሚያቀርብላቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ወላጆች ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ በ2013 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የወላጆች ክትትል አናሳ እንደነበርም አስታውሰዋል።
የዘንድሮው የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከ520 ሺ በላይ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ከ194 ሺ በላይ ተማሪዎችን ያካትታል።