የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት የሚያጸና በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡
የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባላት የስምምነቱን አጠቃላይ ሂደትና ቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ለሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች፣ ለክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ለከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ለብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኮሚቴው አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት÷ ስምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ስምምነቱ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መጠናቀቁን ጠቁመው÷በዚህም
በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ሁለት የታጠቀ ሃይል ሊኖር እንደማይችልና ህግ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበር እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ከህገ-መንግስት ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች ቆመው በትግራይ ክልል በህገ-መንግስቱ መሰረት ምርጫ እኪካሄድ ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡
ያለን አማራጭ እና መፍትሄ በጋራ ተሳስሮ መሄድ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን÷ ከዚህ አኳያ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ቀደመው ማህበራዊ ትስስር እንዲመለሱ በጋራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የደረሰው ጉዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከዚህ አኳያ የወደሙ ተቋማትን ጨምሮ የመልሶ ግንባታ ስራዎች በጋራ ርብርብ ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል፡፡
የትስስርና የተግባቦት ስራዎችም የህዝቦችን መጻኢ የጋራ ጉዞ ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ያሉንን አቅሞች በማስተባበር ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
በግጭቱ ምክንያት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሌሎች መስኮች የደረሰውን ጫና በማስተካካል ረገድም በትብብር መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከዚህ ረገድ በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ቁርሾዎችን ማባባስ ሳይሆን ዜጎች ከችግሩ ተምረው በቀጣይ አብሮነታቸውን አጠናክረው የሚሄዱበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በግጭቱ የተጎዳችው የሁላችንም የጋራ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ናት ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን÷ በመሆኑም ስምምነቱ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ እድል እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኣካላትን ደግሞ በጋራ ማስቆም እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሁሉም ዜጋ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ አኳያ መድረኩ የቀጣይ ስራዎች ትብብር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡