አቶ ጥራቱ በየነ በዛሬው እለት ጳጉሜ 1 ቀን በአገር አቀፍና በከተማ ደረጃ እየተከበረ ያለውን የበጎ ፈቃድ ቀን አስመልክቶ በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሬሄንሲብ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው ታካሚዎችን ጎብኝተዋል።
ታካሚዎች ጤንነታቸው ተመልሶ ድነው ከሆስፒታል እኖዲወጡ መልካም ምኞታቸውንም ገልፀውላቸዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ ጥራቱ በየነ እኛ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህል አለን፣ የተቸገረን መደገፍ፣ የታመመን መጎብኘት ልምድ አለን፣ ለበጎ ስራ ደግሞ በቀዳሚነት የሚያስፈልገው መልካም ልብ ብቻ ሲሆን በጎነት ለራስ ጤንነት የሚሰጥ ፤ በፈጣሪ ዘንድም ውድ ዋጋ ያለው ነው ሲሉም አክለዋል ።
አያይዘውም በጎ ፈቃደኝነት አንድ ቀን ብቻ አስበነው፤ ተናግረነው ወይም አክብረነው የምናሳልፈው ሳይሆን አመቱን ሙሉ እየሰራን ፣ ትውልድን በአስተሳሰብ ፣ በስነምግባርና በባህል እያተጋን አገርን ለብልፅግና የምናደርስበት መንገድ ነው ሲሉም አስምረውበታል ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የበጎ ፈቃደኛ ዜጎች ተሳትፎ እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ጥራቱ በየነ በዚህም በርካታ የከተማችን ወጣቶች፣ ነዋሪዎች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለተቸገሩ ማዕድ በማጋራትና በመሳሰሉት ትውልድን በመቅረፅና ህፃናትን በጎነትን በተግባር በማስተማር መልካም ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ የማድረጉ ሂደት መልካም ውጤት እያመጣ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል ።
በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልም ሆነ በሌሎች የጤና ተቋማት እያገለገሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ዘወትር የታመሙና የተቸገሩ ወገኖቻችን ሙያዊ አገልግሎት የሚሰጡና የሚረዱ የበጎ ፈቃድ ጀግኖቻችን ናቸው ሲሉ አወድሰው በየእለቱ ለታካሚዎች የሚያደርጉት እንክብካቤና ድጋፍ የበጎነት አንድ ማሳያ ስለሆነ ምስጋናና ክብር እንደሚገባቸው አቶ ጥራቱ በየነ በአፅንኦት ገልፀዋል።