የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፥ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የ2015 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀምና ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ እንዲሁም የ2016 አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል።
በተጨማሪም የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር እና አገራዊ ሁኔታ ላይም መምከሩንም ነው የተናገሩት።
በምርጫ ወቅት ፓርቲው ለህዝብ ቃል ከገባቸውን እና በመጀመሪያው የፓርቲው ታሪካዊ ጉባኤ በተቀመጡት አቅጣጫዎች አፈጻጻምን የገመገመ ሲሆን፤ ከዚህም በመነሳት የ2016 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል።
በውይይትም በፓርቲው ውስጥ አባላቱ የጋራ አመለካከት እንዲይዙ ከማድረግ አንጻር ውጤት መመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፤የአመራር ዲሲፕሊን መሻሻል ማሳየቱንና የመፈፀምና ማስፈፀም አቅም እየጎለበተ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የፓርቲውን ተቋማዊ አቅም ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን እና በቀጣይም የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።፡
እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጠናከርና ክፍተት ለመሙላት እንዲሁም በሁሉም የታቀዱ ስራዎች በወጤት እንዲፈፀሙ የአመራር አቅም ለማጠናከር አቅጣጫ መቀመጡንም አንስተዋል።
ሰላምና ፀጥታን በተመለከተም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ ሀይሎች በውይይት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ መቻሉን ገልጸዋል።
ይሁንና የተዛቡ ትርክቶች እና ከፖለቲካ ባህላችን ኋላቀርነት የሚመነጩ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱን የገለጸው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ነገር ግን አመራሩና የጸጥታ ሃይሉ በወሰደው ብልሃት የተሞላው እርምጃ ዓላማን በሃይል ማሳካት እንደማይቻል ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት የተሰራው የተቋም ግንባታ ስራ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ነው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙንም ተናግረዋል።፡
ለአብነትም የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ግንባታ ስራ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟል።
ህዝቡ ለመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ያነሳው ስራ አስፈጻሚው፤ በቀጣይ ችግሮችን በንግግርና ውይይት መፍታት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተጨማሪም ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጎለብት፤ አካታች ሀገራዊ ምክክሩ እና የሽግግር ፍትህ እንዲሳካ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡
ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
በኢኮኖሚው መስክም በግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማደሳደግ የተሰራው ስራ ውጤት ማምጠቱን የተገለጸ ሲሆን፤ ለአብነት በስንዴ፣ በቡና ሻይና አትክልትና ፍራፍሬ በእንስሳት ሀብት ልማት የተመዘገበው ስኬት ለዚህ ማሳያ መሆኑን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል።
አረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት በስኬታማነት እየተሰራ መሆኑ፣ የስራ ፈጠራ እንዲሁም በወጪ ንግድና ገቢ ምርቶችን በመተካት ረገድ ስኬት መመዝገቡንም ኮሚቴው በጥንካሬ ገምግሟል።
በኢትዮጵያ ታምርት መርሃ ግብር በማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የነበሩባቸው ችግሮች ተፈትተው የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ መደረጉ፣ በርካታ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማስቻሉ፣ ምርትና ምርታማነት ማደጉ በመስኩ የተመዘገበ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነቱን መቅረፍ ላይ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ነው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ያስቀመጠው።
በዲፕሎማሲው መስክም ከተለያዩ አገራት ያለው ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ከማድረግ ባሻገር አዳዲስ ወዳጆች ማፍራት መቻሉንም ስራ አስፈጻሚው መገምገሙን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል መቻሏ በዲፕሎማሲው መስክ የተመዘገበ ድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ የዲፕሎማሲ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም እንዲሁ።
በተለይ የህዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸው አገልግሎቶች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አገልግሎት የማዘመንና የተቋም ግንባታ ስራ የማጠናከሩ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራም ስራ አስፈጻሚው አቅጣጫ ማስቀመጡን አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።