ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ታሪክ የሚቀይሩ ወርቃማ የለውጥ ዕድሎች ገጥመዋታል። ፖለቲካችንን አንድ ደረጃ ወደፊት የሚያስፈነጥሩና ቀጣይ ዘመናችንን ብሩህ የሚያደርጉ አያሌ የለውጥ ችቦዎች ተለኩሰዋል። እነዚያ ለውጦች የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ ቁጭት። በቁጭት ተጠንስሰው፣ በቁጭት ተካሂደው፣ በቁጭት ይጠናቀቃሉ። አብዛኛውን ጊዜ የለውጥ ምዕራፎች በሚጀምሩበት ወቅት የምንሰንቃቸው የለውጥ ሐሳቦች ዳር ከመድረሳቸው በፊት ሲኮሰምኑ በተደጋጋሚ አይተናል። በለውጥ በሂደት ወቅት ግባችንን ለማሳካት ከመተባበር ይልቅ በጥቃቅን ጉዳዮች እርስ በእርስ መጓተቱን ስለምናስቀድም በመጀመሪያ ያስጎመጅ የነበረው የለውጥ ፍሬ በመንገዱ መሐል ተጨናግፎ ይቀራሉ። መጨናገፋቸውን ልብ የምንለው ዘግይተን በመሆኑ ዕድሎቹ ካለፉ በኋላ እንደ ሀገር መልሰን እንቆጭባቸዋለን።
እኛ የቀደመውን ትውልድ “ይሄንና ያንን ቢያደርግ ኖሮ” እያልን እንደምንወቅሰው ሁሉ፣ የቀደመው ትውልድም ከእሱ በፊት የነበረውን ትውልድ ሲኮንን ነበር። ከዚህ የታሪክ አዙሪት ለመውጣት እስካልወሰንን ድረስ ነገ የእኛም ዕጣ ካለፈው የተለየ አይሆንም። ዛሬ በቸልታ የምናልፋቸው አጋጣሚዎች ተደምረው ነገ ላይ የልጅ ልጆቻችን እኛን የሚወቅሱበት ምክንያት ይሆናል። ይህ እንዳይሆን ዛሬ እጃችን ላይ የሚገኙ የለውጥ ዕድሎችን ሁሉ አሟጥጠን ለመጠቀም መረባረብ አለብን።
ለዘመናት እየተንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ የፖለቲካ ፈተናዎቻችንን በጉልህ መቅረፍ የሚያስችለንና መጻዒ ዘመናችንን አዲስ መሠረት ላይ የማቆም ዐቅም ያለው ብሔራዊ የምክክር ሂደት ዛሬ በእጃችን ላይ ያለ ወርቃማ ዕድል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህን ወርቅ የሆነ አጋጣሚ የስንት ልፋት እና የስንት ታሪክ ሂደት ውጤት መሆኑን ዘንግተን እንደ ጠጠር ከቆጠርነው በቀላሉ ልናጣው እንችላለን። በተቃራኒው እንደ ዕንቁ አክብረንና ተከባክበን ከተጠቀምንበት ዋጋው ከፍ ያለና ታሪክ ቀያሪ ዕድል ይሆናል። ልጆቻችንም “አባቶቻችን እንዲህ በማድረጋቸው ሀገራችን እዚህ ከፍታ ላይ ደርሰች” ብለው የሚያመሰግኑበትን አጋጣሚ ይፈጥራል።
አካታች ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሒደቱ ተቀባይነት ያለው ሆኖ መከናወን አለበት። ይኽም የሚሆነው ሁላችንም የምክክር ሂደቱን በበላይነት የሚመራውን የምክክር ኮምሽን በተለያዩ መንገዶች መደገፍ፣ ማትጋትና ማጽናት ስንችል ነው። በዚህ ጉዳይ ዳር ቆሞ መገኘት በታሪክ ፊት የሚያስወቅስ ተግባር ነው። ሁሉም አካል በባለቤትነት ስሜት ለምክክር ሂደቱ አስተዋጽዖ በማድረግ ተሳትፎውን ያረጋግጣል እንጂ አንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ከታሪክ ተጠያቂነት ነጻ አያደርግም።
በመንግሥት በኩል እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን በቅልጥፍና መሥራት እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም። የክልል መስተዳደሮች ቀናነት፣ ባለቤትነትና ታሪካዊ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለኮሚሽኑ ሥራ አስፈላጊ የሆነውን ግብአት በማቅረብ ለሥራው ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይገባል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በውይይቱ እንደሚሳተፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ሂደቱ ባለቤት ለሂደቱ ቅልጥፍናና ስኬት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ በትኅትና እጠይቃለሁ።
ምሁራን ኮሚሽኑ አስተያየትና ምክረ ሐሳባችሁን በሚፈልግበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ ተነሣሽነት፤ የሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የታሪካዊ ጉዟችን እና የዘመን አሻራችን ለሆነው ምክክር አስተዋጽዖዋችሁ የላቀ እንዲሆን እማጸናለሁ። የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሀገር ስምምነትን በምትፈልግበት በዚህ ወቅት አማካይ ሆናችሁ ሁሉን የማስማማት አደራ አለባችሁና የመቀራረቢያውን መድረክ በማገዝ ሀገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ከልብ በመነጨ ትኅትና እጠይቃለሁ።
የሁሉም ኃላፊትነት ተደምሮ የሚወድቀው በሀገርና በሕዝብ ትከሻ ላይ ነው። ሁላችንም ልዩነቶቻችንን አቻችለን በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ አለብን። ሕዝብ ያላከበረው እና ሕዝብ ያልደገፈው እንቅስቃሴ ውጤቱ መና ነውና መላ ኢትዮጵያውያን ድጋፋችሁ፣ ተሳትፏችሁ፣ክብራችሁና ጸሎታችሁ ከኮሚሽኑ እንዳይለይ ከታላቅ አክብሮት ጋር እጠይቃለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!