የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው እለት ውይይት አካሂደዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት ቡድን እና ተላላኪዎቹ ኢትዮጵያን እኔ ካልመራዋት ትፍረስ ፤ትበታተን የሚል አላማን አንግበው እየሰሩ መሆናቸውን ሁሉም በሚገባ ሊገንዘብ እና ሊያውቅ ይገባል፡፡
ይህን የተደቀነብንን ሀገር የማፍረስ አደጋ ለመቀልበስ ሁሉም አመራር ተቀናጅቶ ፣ ተናቦ እና የተግባር አንድነት ፈጥሮ ሀገርን ከብተና ኢትዮጵያዊያንን አገር አልባ ከማድረግ ክፉ ምኞት መታደግ እንዳለበት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እና መላው ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች የጸጥታ አካላትን በሞራል እና በሎጅስቲክ በመደገፍ ደጀንነቱን ማሳየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ወጣቶችም እንደከዚህ ቀደሙ የመከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሀገራዊ ለውጥ በፅንፈኛ ቡድኖች እንዳይቀለበስ መታገል እንዳለባቸው ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል ።
ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የአሸባሪውን ተላላኪዎች በተደራጀ መንገድ በማጋለጥና አሳልፎ በመስጠት የአካባቢዉን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ እና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በትኩረት መሰራት እንደሚገባም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል ፡፡