“ተግዳሮት ያልበገረው ለውጥ፣ በአዲስ አበባ!” በሚል ርዕስ ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራር የ2015 ዓ.ም አፈፃፀም ግምገማ ላይ ይገኛል።
የግምገማ መድረኩን አጠቃላይ ሂደት አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ዛሬ ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ የፓርቲ እና የመንግስት የልማት ስራዎች ዕቅድ አፈፃፀም መድረክ በ2016 ዓ/ም ከዘንድሮውም የበለጠ ስኬት በማስመዝገብ የህዝባችንን ተስፋ እና እምነት ወደ ተግባር ለመለወጥ የአስተሳሰብ አንድነትና የጋራ ተልዕኮ ይዘን የምንወጣበት መድረክ ነው ብለዋል።
አቶ ሞገስ አክለውም የተጠናቀቀው የ2015 ዓ/ም በጀት ዓመት ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከመምህራን፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ የተነሱ ሀሳቦችን የከተማ አስተዳደሩ ዕቅድ አካል በማድረግ ህዝባችንን አሳትፈን በመስራታችን በሰላም፣ በልማት እንዲሁም በመልካም አስተዳደር አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የተጠናቀቀው 2015 ዓ/ም በጀት ዓመት በዕውቀት፣ በጉልበት እንዲሁም በገንዘብ የህዝቡ ተሳትፎ ጎልቶ የወጣበት ነው ያሉት ኃላፊው ከተሰሩ እና ተመርቀው ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲውል ከተደረጉት ፕሮጀክቶች ገሚሱ በህዝብ ተሳትፎ መሰራታቸው ለዚህ ማሳያም ብለዋል።
ብልሹ አሰራርን ታግሎ ለማስተካከል እና እየተሻሻለ ያለውን አገልግሎት አሰጣጥ ከሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በ2016 ዓ/ም የፈፃሚን አቅም በማሳደግ ከዘንድሮውም የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ ሰባቱንም ቀን 24 ሰዓት እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ሞገስ እየተደረገ ያለው ግምገማዊ ውይይት የህዝባችን ተስፋ እና እምነት ወደ ተግባር ለመለወጥ የአስተሳሰብ አንድነትና የጋራ ተልዕኮ ተይዞ የሚወጣበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች ከተማ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ተቻችሎና ተከባብሮ ለዘመናት ተጋምዶ የኖረውን ህዝብ ለመነጣጠል በማህበራዊ ሚዲያው የሚያረግቡ ፅንፈኞችና አክራሪዎች ሰሚ ባያገኙም ፣ በሀሰት ትርክት ዕኩይ የጥላቻ መርዝ በመርጨት አብሮነትን መሸርሸር ላይ አነጣጥረው እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞገስ በቀጣይም ብልፅግና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ፓርቲ እንደመሆኑ የአብሮነት ዕሴታችንን በማጎልበት፣ ህዝቡን በማሳተፍ እኩይ ሴራቸውን የማክሸፍ ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።