“ታላቁ ህዳሴን ለመገንባት ሳናጠና አልገባንም፤ ሳንጨርስ አናቆምም፤የብልጽግና ጉዟችን በህዳሴ ምእራፍ ውስጥ የሚደምቅ የከተማችን ብሎም የሀገራችን ብርሃን ነው”ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤበዋንጫ ሽኝት መርሐግብር ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ማደሪያ ላልነበረው ዓባይ ማደሪያውን ላበጃችሁ፤ ከታሪክ ተናጋሪነት ወደ ታሪክ ሰሪነት ላሸጋገራችሁን ፣ በአለም አደባባይ ለአባይ ሞግታችሁ፣ የጉባ በረሃ ንዳድን ተቋቁማችሁ፣ በክብር ከዚህ መድረክ ላይ እንድንቆም ላበቃችሁን ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ከልብ የሆነ ምስጋናን አቀርባለሁ ብለዋል ፡፡ውድ የአገሬ ልጆች፤ በተለይም የአዲስ አበባችን ነዋሪዎች፤የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች የማመስገኛውን ቃል በተግባር በወርቅ ቀለም ስለጻፋችሁ፣ ከስንዝር እስከ እርምጃ፡ ሳትሰስቱ ለታላቅነታችን መገለጫ ለህዳሴ ግድባችን አሻራችሁን ማስቀመጥ በመቻላችሁ ነው ብለዋል ወ/ሮ አዳነች ፡፡ዓባይ ወንዝ ብቻም አይደለም ይልቁንም አገር ነው ምክትል ከንቲባዋ ህዳሴ ግድብ ብቻም አይደለም ይልቁንም የኢትዮጵያ መድመቂያ አርማና ኩራት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።ዓባይ ስም ብቻም አይደለም አሻጋሪ ሃሳብም ነው ፤ ዓባይ ብርሃን ብቻም አይደለም ምግብም ነው ለዚህም ነው “እራትም መብራትም” ነው የምንለው ሲሉ ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል ።

የህዳሴ መነሻው ነገን ጭምር የማየት ብቃት ነው፡፡ መድረሻው ደግሞ የመላ ኢትዮጵያዊያን እና የከተማችን ነዋሪዎች ብልጽግና ነው ብለዋል ፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት ሳናጠና አልጀመርንም ፤ ሳንጨርስ አናቆምም ያሉት ወ/ሮ አዳነች የብልጽግና ጉዟችን በህዳሴ ምእራፍ ውስጥ የሚደምቅ የሀገራችንና የከተማችን ብርሃን ነው ብለዋል ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ3 ቢሊዩን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ በ6 ወራት ብቻ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ የቀጣይ ተረኛ ለሆኑት ሐረሪ ክልል እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በይፋ ተሸኝተዋል ።በሽኝቱ በቦንድ ግዢ እና በሌሎች ተግባራት አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሀብቶች፣ ተቋማት እና አካላት የምስጋና እውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል::