እስከ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓም ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቀየው 2ኛው ዙር ከተማ አቀፍ የሕብረት ስራ ማኅበራት ኤግዚብሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ከተማ ገበያ ልማትና ኤግዚብሽን ማዕከል በከንቲባ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በዛሬው እለት ተከፈቷል፡፡
ከ1.5 ሚሊዮን በላይ አባላት ያላቸው የኅበረት ስራ ማኅበራት በአዲስ አበባ ከተማ እየተንቀሳቀሱ ሲሆን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ከአምራቹ በቀጥታ በመረከብ በተመጣጠነ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ የዋጋ ንረቱን በማቅለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ከማበርከታቸው ባሻገር በብድርና ቁጠባ ማኅበራት በኩል በአነስተኛ ስራ ዘርፎች ለተሰማሩ ዜጎች ብድር በማቅረብ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡
የከተማው ህዝብ ህገ ወጦች በሚፈጥሩት አርቴፊሻል የፍጆታ ዕቃዎች ዕጥረት ሳቢያ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ብር በተዘዋዋሪ ፈንድ ለህብረት ስራ ማኅበራት ድጋፍ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡ የኅብረት ስራ ማኅበራቱ ከተማ እና ገጠርን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የነበራቸው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት የህዝቡን የኑሮ ሸክም ማቅለል መቻላቸውንና አውስተዋል፡፡
አምራቹን ከሸማቹ ለማስተሳሰር የሚያስችሉ በአምስቱም የአዲስ አበባ በሮች ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ወጥቶባቸው በከተማ አስተዳደሩ እየተገነቡ ያሉ የግብርና ውጤቶች ገበያ ማዕከላት የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል በማቅረብ የህዝቡን የኑሮ ጫና ለማቅለል ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለው ገልጸዋል፡፡
አቶ አደም ኑሪ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የኅብረት ስራ ማኅበራት ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ የአሰራርና አደረጃጀት ችግሮቻቸውን መፍታት የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች በከተማ አስተዳደሩ መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው የተዛባ የገበያ ስርዓት፣ ሕገ-ወጥ ንግድና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ሳቢያ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ህብረት ስራ ማኅበራትን ማጠናከር የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል መደረጋቸውን አቶ ግዛቸው አሊ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ስራ ማኅበራት ኤጀንሲ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡