የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የትምህርት እና የጤና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሁሉም ክ/ከተሞች ያስገነባቸውን 100 ፕሮጀክቶች በነገው ዕለት ያስመርቃል::
የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ ባለፈው በጀት ዓመት አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባትን ጨምሮ የማስፋፋት እና የእድሳት ስራዎች የተሰሩባቸው የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በመጪው የ2016 ዓ/ም የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።
ከት/ቤቶች በተጨማሪ በነገው ዕለት የሚመረቁት ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ጤና ተቋማትም የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን አዳጊ ፍላጎትና መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ማሳያ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ እናታለም መለሰ የገለፁ ሲሆን ባለሀብቶችን እና አጠቃላይ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ዓመትም ከአጠቃላይ 140 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 70 ቢሊዮን ለካፒታል በጀት ሲሆን ትምህርት፣ ጤና እና ውሀ ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ተብሏል።