የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ለማሳካት የሚጥሩትን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በጋራ መመከት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ተገዶ የገባበትን ጦርነት በድል ለመወጣት ሲቃረብ እንቅልፍ የሚያጡ፤ የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት መንገድ የተሳካ ሲመስላቸው “ግፋበት” በማለት በይፋ የሚናገሩ ታሪካዊ ጠላቶች እንዳሉ ይታወቃል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ መለሰ ዓለሙ፤ የአሸባሪውን የጥፋት እንቅስቃሴ በግልጽና በስውር የሚደግፉ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንዳሉ ይናገራሉ።
በዚህም አሸባሪው ሕወሓት የጦርነት እንቅስቃሴው የተሳካለት ሲመስላቸው ዝምታን መርጠው እያበቃለት ነው ብለው ሲያስቡ ደግሞ ለማትረፍ የሚረባረቡ ጠላቶች አሉ ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረበትና ህዝቡን እየገደለና መሰረተ ልማትን እያወደመ ደብረሲና በደረሰበት ወቅት ከውስጥና ከውጭ ያሉ የጥቅም ተጋሪዎቹ ድምጻቸውን አጥፍተው መደገፋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው አከርካሪውን ተመትቶ ወደመጣበት ሲመልስ ደግሞ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ ያሳስበናል በማለት “የሰላም አምባሳደሮች” መስለው ለመታየት ያደረጉትን ጥረት አስታውሰዋል።
የዚህ ሁሉ ስውር ዓላማ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ ያሰበው እንዲሳካ ለማድረግ መሆኑን አቶ መለሰ ተናግረዋል።
በመሆኑም በትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጥረት የሚያደርጉ የአሸባሪው ቡድን አባላትና ተባባሪዎቻቸውን ተግባር ማጋለጥና በጋራ መታገል የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን፣ የግዛት አንድነታቸውን፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ክብራቸውን ለማስጠበቅ እየሄዱበት ያለው እርቀት ተፈጥሮአዊ መብታቸው ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይት በአሸባሪው ህወሃት የትግራይ ህዝብ ያልተገባ መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ተናግረዋል።
የቡድኑን ፍላጎት እንደማያውቁትና እንደማይረዱት የተናገሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች ለፖለቲካ ጥቅም ከሌሎች ወንድም ህዝቦቹ ለመነጠል የሚደረገው ጥረት ፈፅሞ የማይሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ቡድንና የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ ባንዳዎች በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ መለሰ፤ በጋራ ታግሎ ማሸነፍ ይገባል ብለዋል።
ከትግራይ ተወላጆች ጋር በቅርቡ የተደረገው ውይይት ቀጣይነት የሚኖረው መሆኑን ተናግረው፤ አሸባሪውን ከህዝቡ ትከሻ ላይ ለማውረድ የጋራ ትግል እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በተለይ የትግራይ ህዝብ የታፈነውን ወገኑን ለመታደግ የጀመረውን ሁለንተናዊ ትግል አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት