የአሸንዳ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና የክብር እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኢፌዴሪ ባሕልና ቱሪዚም ሚኒስትር ዶ/ር ቀጀላ መርዳሳ ፣ የኢፌዴሪ ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ድክተር/ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በክብረ-በዓሉ ላይ ታድመዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በክብረበዓሉ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ውብ ባህላዊ እሴቶች : ትውፊቶችና ድንቅ ማንነቶች ህብር የሆነች ሃገር ናት ያሉ ሲሆን ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ፤ አስደናቂ ሃገራዊ ጥበባት : ወጎችና ባህሎች ያሏት ታይታ የማትጠገብ አስደናቂ ሃገር ናት ብለዋል፡፡
አዲስ አበባም የሁላችን ከተማ ናት ያሉት ከንቲባዋ አዲስ አበባ ያለማንነት ልዩነት ሁሉም ፤ተሳስቦ የሚኖርባት ፤ ለሁላችን ቤት እንጂ ማንንም ባይተዋር የማታደርግ ከተማ ነች ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እንደ ከንቲባ አዳነች አባባል አዲስ አበባ ቤታችሁ ናት ፤ ለዚህም ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች : በየአካባቢው የአሸንዳን በአል በፍቅር፤ በአብሮነት አብሯችሁ እያከበረ ያለው ብለዋል፡፡
የአሸንዳ በአል የሰላምና የሰላም ወዳዶች በዓል ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች የአሸንዳ ልጃገረዶች የሰላም አምባሳደሮችና የሰላም ወዳድነት ህያው ተምሳሌቶች ናቸው ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆምን፤ ሊያለያዩን የሚፈልጉ አካላትንና ፤ብሎም የውጪ ሃይሎች ጫናዎችን ሁሉ በከፍተኛ ብስለትና አስተዋይነት ያለፍን ፤ ፈተናን እና ፈታኞችን ደጋግመን ያሳፈርን ህዝቦች ነን ብለዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ጥላቻና መከፋፈል ይብቃን ያሉት ከንቲባዋ ለትውልድ የመለያየትና የግጭት ክፉ ውርስን አናውርስ ፤በጥላቻ ዘላቂ አሸናፊነት የለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋቻቸው እጆች አልታጠፉም ያሉት ከንቲባ አዳነች ችግሮችና ልዩነቶች በጠመንጃ ዘላቂ መፍትሄ አያገኙም ሲሉም ገልፀዋል፡፡
አሸንዳ ማሕበራዊ ፋይዳው ሕዝቦችንና ኢትዮጵያውያን ከማስተሳሰር አንጻር ሚናው የላቀ በመሆኑ በአሸንዳ በዓል አከባበር ውስጥ የሚገለጹ ዕሴቶችን አውጥተን በመጠቀም አንድነታችንና ማህበራዊ ትስስራችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ያሉት የኢፌደሪ ባሕልና ቱሪዚም ሚኒስትር ዶ/ር ቄጄላ መርደሳ ናቸው።
የአዲስ አበባ የአሸንዳ በአል አከባበር ኮሚቴ ሰብሳቢ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የቤቶች ልማት ቢሮ ሀላፊ ወ/ት ያስሚን ዋሀቢረቢ እንደተናገሩት የአሸንዳ በዓል በትግራይ ማህበረሰብ የፍቅር፣ ሰላም እና የመልካም ተግባቦት በተግባር የሚንጸባረቅበት በዓል ከመሆን በተጨማሪ
ከሀገራችን አልፎ ለአለም ቅርስነት የሚበቃ የማይዳሰስ የኢትዮጵያዊያን ሃብት በመሆኑ ባህሉን ጠብቅን በማክብር ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ የበኩላችንን እንድንወጣ በዚሁ አጋጣሚ እጠይቃለሁ ብለዋል።